“ሰራዊቱ በተሰጠው ህዝባዊ አደራ ልክ ህግን የማስከበርና የወንጀል መከላከል ስራውን በላቀ ዲስፕሊንና ብቃት ሊወጣ ይገባል” ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር)

“ሰራዊቱ በተሰጠው ህዝባዊ አደራ ልክ ህግን የማስከበርና የወንጀል መከላከል ስራውን በላቀ ዲስፕሊንና ብቃት ሊወጣ ይገባል” ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር)

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ለስራ ጉብኝት የበረሃዋ ገነት ወደሆነችው ሰቲት ሁመራ ከተማ በመሄድ ከዞኑ የፖሊስ ሰራዊት ጋር ፍሬያማ ውይይት አካሄዱ።

ኮሚሽነር ጀኔራሉ ሁመራ ከተማ ሲደርሱ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

በስነ-ስርዓቱ ላይ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሸተ ደምለው፣ የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ እና የሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ፣ የዞኑ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ወለላው ተገኘ እንዲሁም የዞን እና የወረዳ የፖሊስ አመራሮችና አባላት ተገኝተዋል።

የኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) የጉብኝት ዋና ዓላማ በክልሉ ፖሊስ እየተተገበረ ያለው የሪፎርም ስራ አካል የሆኑትን የዞንና የወረዳ የፖሊስ ፅህፈት ቤት የቢሮ ግንባታዎችን፣ የቢሮ እድሳትንና የፖሊስ ሰራዊቱን አጠቃላይ ቁመና መመልከትና መገምገም ነው።

በዚህም መሰረት ኮሚሽነር ጀኔራሉ በዞኑ እየተገነቡና እየታደሱ ያሉ የፖሊስ መሰረተ ልማቶችን እና የስራ ሁኔታቸውን በቅርብ የተመለከቱ ሲሆን፤ ከዞኑ የፖሊስ ሰራዊት አመራሮችና አባላት ጋር በወቅታዊ የጸጥታ እና ደህንነት ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ምክክርና ውይይት አካሂደዋል።

በጥልቀት በተካሄደው በዚህ መድረክ ላይ ከተሳታፊዎችና ከአመራሮች የተለያዩ ሃሳቦችና ጥያቄዎች ተነስተው ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

የዞኑ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ወለላው ተገኘ በውይይቱ መጀመሪያ ላይ ባቀረቡት ሪፖርት እንደገለጹት የዞኑ የፖሊስ ሰራዊት አካባቢውን አስተማማኝ ሰላም ለማድረግ ሌት ተቀን እየሰራ ይገኛል።

አዛዡ አክለውም የሰራዊታችንን አቅም በስልጠና እና በትጥቅ በማጠናከር ረገድ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ ቢሆንም የሪፎርም ስራዎችን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የተጀመሩ የቢሮ ግንባታዎችና የመሠረተ ልማት ማሻሻያዎች በፍጥነት መጠናቀቅ አለባቸው ብለዋል።

የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ እና የሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ በበኩላቸው የፖሊስ ሰራዊቱ ከአካባቢው ማህበረሰብና ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት እያከናወነ ያለው የሰላም ማስከበር ስራ የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሰላምን በአስተማማኝ ሁኔታ ዘላቂ ለማድረግ የጸጥታ መዋቅሩን ዝግጁነትና ቁመና በየጊዜው ማሳደግ ወሳኝ ነው፤ የዋናው መምሪያ ድጋፍም ይህንን አቅም ይበልጥ ያጠናክረዋል የሚል እምነታቸውን አክለው ገልጸዋል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሸተ ደምለው ባደረጉት ንግግር የክልሉ ፖሊስ አመራር ለዞኑ እየሰጠ ላለው ትኩረት ምስጋና አቅርበው የዞኑ አስተዳደር ለፖሊስ ተቋማዊ ሪፎርም ስኬታማነትና ለመሰረተ ልማት ግንባታዎች አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደማይለይ አረጋግጠዋል።

የተነሱትን ሃሳቦችና ጥያቄዎች መሰረት በማድረግ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ለሰራዊቱና ለአመራሩ ሰፊ የስራ መመሪያና አቅጣጫ ሰጥተዋል።

ኮሚሽነር ጀኔራሉ ባስተላለፉት መልዕክት የህዝባችንን ሰላምና ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለማስከበርና የፖሊስ ተቋማዊ ሪፎርሙን ዳር ለማድረስ የሰራዊቱ ዝግጁነትና ቁርጠኝነት ከፍተኛ ሚና አለው ብለዋል።

“ሰራዊቱ በተሰጠው ህዝባዊ አደራ ልክ ህግን የማስከበርና የወንጀል መከላከል ስራውን በላቀ ዲስፕሊንና ብቃት ሊወጣ ይገባል” ሲሉ ኮሚሽነር ጀኔራሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የተጀመሩ የቢሮ ግንባታዎችና እድሳቶች የፖሊስን የስራ አካባቢ በማሻሻል ለህዝቡ የሚሰጠውን አገልግሎት ቀልጣፋ እንደሚያደርጉት ገልጸው፣ ዋና ጠቅላይ መምሪያው የሰራዊቱን የሎጅስቲክስ፣ የትጥቅና የህክምና አገልግሎት ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በመጨረሻም በውይይቱ ላይ የዞኑን ሰላምና ጸጥታ ይበልጥ ለማጠናከር፣ የህግ የበላይነትን ለማስከበር እና የጸጥታ መዋቅሩን አቅም በቴክኖሎጂና በሰው ሃይል ለማሳደግ በሚያስችሉ ቀጣይ ቁልፍ አቅጣጫዎች ላይ የጋራ መግባባት ላይ መደረሱ ተገልጿል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top