በግዳጅ መስመር ላይ አካላቸውን የሰጡ ጀግኖች ተቋማቸው ከጎናቸው መሆኑን ያረጋገጠ ልዩ የጉብኝትና የድጋፍ ስነ-ስርዓት ተከናወነ።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የሀገራቸውን ደህንነት ለመጠበቅ፣ የህግ የበላይነትን ለማስከበርና የህዝብን ሰላም ለማረጋገጥ በግዳጅ መስመር ላይ እያሉ የአካል መስዋዕትነት ለከፈሉ የጸጥታ ኃይል አባላት አጋርነቱን የሚገልጽ የማበረታቻና የድጋፍ መርሃ-ግብር አካሄደ።
ይህ የድጋፍና የጉብኝት ስነ-ስርዓት የተከናወነው በአዲስ አበባ በሚገኙት በጦር- ኃይሎች ሆስፒታል፣ በኢትዮጵያ ፖሊስ ሆስፒታል እና በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ጀግኖች ማገገሚያ ማዕከል ህክምናቸውንና ማገገሚያቸውን በመከታተል ላይ ለሚገኙ የሀገር ባለውለታዎች ነው።
በቦታው ላይ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ከፍተኛ አመራሮች በአካል በመገኘት ጀግኖቹን የጸጥታና የሰላም አስከባሪ አባላት የጠየቁ ሲሆን፣ የተዘጋጀውንም ተቋማዊ ድጋፍ በክብር አስረክበዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ማህበራዊ አገልግሎት መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር አየሁ ታደሰ እንደገለጹት፣ ክልሉ በከባድ የፀጥታ ችግር ውስጥ በነበረበት ወቅት ሀገርን ለጠላት አሳልፎ ላለመስጠት የተደረገው ተጋድሎ በታሪክ መዝገብ ላይ በወርቅ ቀለም ተመዝግቦ እንደሚኖር ገልጸዋል።
“አካላችሁን የሰጣችሁት ለሀገር ፍቅርና ለህዝባችሁ ደህንነት ሲባል ነው ያሉት ኃላፊው እናንተ በጣም ጠንካሮችና የክልላችን እውነተኛ አምባሳደሮች ናችሁ”ብለዋል።
ረዳት ኮሚሽነር አየሁ አክለውም፣ ይህ ተግባር በተለያዩ ግንባሮች በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ ለተሰማሩ ሌሎች የጸጥታ አባላት ላገለገሉት ተቋምና ህዝብ ዋጋ ማጣት የለም የሚል ጠንካራ ስነ-ልቦናዊ ዋስትና እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የጤና አገልግሎት መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር መሰለ ስዩም በበኩላቸው፣ ለሀገር ሉዓላዊነትና ለህዝብ ዘላቂ ሰላም ሲባል የገዛ አካልን አሳልፎ መስጠት የላቀ የሀገር ፍቅር መገለጫ መሆኑን በመጠቆም የደረሰባቸው የአካል ጉዳት የውድቀት ሳይሆን የክብር፣ የጀግንነትና የታሪካዊ አሻራ ማህተም መሆኑን አስምረውበታል።
የተደረገው ድጋፍ ከተገኘው ቁሳዊ እሴት ባሻገር፣ በትግል ሜዳ ላይ ለቆሰሉ ጀግኖች ትልቅ የሞራል ካሳና የስነ-ልቦና ጥንካሬ የሚሰጥ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ጀግኖች በከፈሉት መስዋዕትነት ልክ ተገቢውን የህክምና እና የአካል ተሃድሶ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ሙያዊ ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን ታሪካዊ ግዴታ ነው ሲሉም ኮማንደር መሰለ ስዩም አረጋግጠዋል ።
ኮማንደር መሰለ አክለውም፣ የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ተገቢውን ክብር፣ ህክምና እና ማህበራዊ ዋስትና እንዲያገኙ ለማድረግ የተለያዩ የለውጥ ስራዎችን በሪፎርሙ አካቶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ፖሊስ ሆስፒታል ጤና አገልግሎት ዋና መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ዶክተር አብርሃም ተፈራ፣ የክልሉ ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች ያደረጉት ጉብኝት ለሀገርና ለህዝብ ደህንነት ሲሉ ከፍተኛ ዋጋ የከፈሉ ጀግኖችን በማገገሚያና በሆስፒታሎች በመገኘት ማስታወስና ማበረታታት፣ የጸጥታው መዋቅር ለሰው ኃይሉ የሚሰጠውን ሰብአዊና ሙያዊ ክብር በግልጽ የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ዶክተር አብርሃም አክለውም፣ ይህ አይነቱ እውቅናና እንክብካቤ ተጎጂዎች የደረሰባቸውን የአካል ጉዳት በጽናት ተቋቁመው ወደ ቀጣዩ የህይወት ምዕራፍ በልበ-ሙሉነት እንዲሻገሩ የሚያግዝ በመሆኑ፣ በህክምናው አንዱና ዋነኛው አካል ተደርጎ ይወሰዳል ሲሉ የጉብኝቱን የስነ-ልቦና ግንባታ ፋይዳ አስገንዝበዋል።
ኮማንደር ዶክተር አብርሃም ተፈራ ጀግኖቻችንን መደገፍና መንከባከብ የሁላችንም የጋራ ኃላፊነት በመሆኑ፣ የምናደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ ይበልጥ አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ አረጋግጠዋል።
ድጋፍ የተደረገላቸው የጸጥታ አካላት በበኩላቸው፣ በዋና ጠቅላይ መምሪያው ከፍተኛ አመራሮች የተደረገላቸውን ጉብኝትና ድጋፍ ተቋሙ ለሀገር ባለውለታዎች ያለውን ከፍተኛ ክብርና ፍቅር በተግባር ያሳየበት ነው ብለዋል።
ለሀገራቸው ደህንነትና ለህዝባቸው ሰላም ሲባል የከፈሉት የትኛውም ዓይነት መስዋዕትነት ኩራት እንጂ ጸጸት የለውም ሲሉም በኩራት ተናግረዋል።
የተከፈለው መስዋዕትነት በከንቱ እንዳልቀረና ተቋማቸውና ህዝባቸው ከጎናቸው መሆናቸውን በማየታቸው ትልቅ ክብርና ኩራት እንደፈጠረባቸውም ጠቁመዋል።
የሆስፒታሉ አመራሮችና የህክመና ባለሙያዎች እያደረጉት ያለው ተከታታይ ክትትልና ድጋፍ ሊመሰገን የሚገባው መሆኑን ጠቅሰው መሰል የጉብኝትና የስነ-ልቦና መድረኮች በቋሚነት እንዲቀጥሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ይህ የጀግኖች አባላት እንክብካቤና ድጋፍ ተቋሙ በአዲስ መልኩ ከጀመረው ዘመናዊ የሪፎርም ስራ ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት ያለው ነው።
በተለይም በደብረ ብርሃን ከተማ በከፍተኛ ፍጥነት በግንባታ ላይ የሚገኘው የጀግኖች ማገገሚያ ማዕከል፣ የክልሉ ፖሊስ ለደከሙለትና ደማቸውን ላፈሰሱለት አባላቱ ያለውን ጥልቅ ፍቅር፣ ክብርና አጋርነት በተግባር ያሳየበት ደማቅ ማረጋገጫ ነው።
ማዕከሉ ሲጠናቀቅም አባላቱ በደረሰባቸው የአካል ጉዳት ከተረጂነት ስሜት ወጥተው፣ በራሳቸው እንዲተማመኑና አዳዲስ የዲጂታል፣ የቴክኖሎጂና የአስተዳደር ሙያዎችን ቀስመው በላቀ አቅም ወደ ስራ እንዲሰማሩ ሰፊ በር የሚከፍትም ይሆናል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የአካል ጉዳት መስዋዕትነት የጀግንነት ማረጋገጫ እንጂ የህይወት ጉዞ ማቆሚያ አለመሆኑን በመግለጽ፣ በቀጣይም የማገገሚያ ማዕከላቱን አቅም በማሳደግ፣ ጀግኖችን በክብር የመንከባከብና ለሀገር ጠቃሚ ዜጋና የፀጥታ ኃይል አድርጎ የማስቀጠል ስልታዊ ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል በድጋሚ አረጋግጧል።



