የአስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያ የ2018 በጀት ዓመት አፈፃፀምን በመገምገም የቀጣይ ዓመት የስራ አቅጣጫዎችን አስቀመጠ።

የአስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያ የ2018 በጀት ዓመት አፈፃፀምን በመገምገም የቀጣይ ዓመት የስራ አቅጣጫዎችን አስቀመጠ።

በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የአስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያ በ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት የስራ አፈፃፀም እና በ2019 ዓ.ም በጀት ዓመት ዕቅድ ዙሪያ የግምገማና የውይይት መድረክ አካሂዷል።

ጠቅላይ መምሪያው በበጀት ዓመቱ የፈፀማቸውን ቁልፍ ተግባራትና ለቀጣይ በጀት ዓመት የያዛቸውን ዕቅዶች የሚያሳይ ዓመታዊ ሪፖርት ቀርቦ ጥልቅ ግምገማና ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በሪፖርቱ ከቀረቡ የበጀት ዓመቱ አንኳር ጉዳዮች መካከልም ብቁ እና ተቋምን መለወጥ የሚችል የሰራዊት ግንባታን በተመለከተ ለተቋሙና ለሙያው ፍቅርና ክብር እንዲኖረው እንዲሁም በሙያው ውጤታማ እንዲሆን በማድረግ በበጀት ዓመቱ ሰፊ ስራ ስለመሰራቱ ተነስቷል ።

ከሰው ኃይል መረጃ አያያዝ በኩልም ቀደም ሲል ከነበረው አድካሚና ያልተደራጀ አያያዝ በመውጣት በቴክኖሎጂ የታገዘ የመረጃ አያያዝ ስርዓትን መከተል መጀመሩም የበጀት ዓመቱ አንኳር ተግባር ነው።

የአመራር ብቃትን ለማጎልበትና ተተኪ አመራሮችን ለማፍራትም በዩኒቨርስቲ ኮሌጁ ከኢንስፔክተር ወደ ዋና ኢንስፔክተር የማዕረግ ሽግግር ስልጠናም በበጀት ዓመቱ ተከናውኗል።

የበጀት ዓመቱ ቁልፍ ተግባር የነበረው የተቋማዊ የለውጥ ስራ እንዲሳለጥ በግዢና ፋይናንስ በኩል የተፈፀሙ የግዥ ስርዓቶች አማካኝነት ሪፎርሙ ግቡን እንዲመታ መደረጉንም በሪፖርቱ ተብራርቷል።

ለመደበኛና በግዳጅ ለተሰማራው የፖሊስ ሰራዊት አዲሱን የደንብ ልብስ እና ሌሎች አስፈላጊ የሎጀስቲክ አቅርቦቶችን በማቅረብ እና በርከት ያሉ ተሽከርካሪዎችን ጠግኖ ወደ ስራ በማስገባት በኩልም በሎጀስቲክስ ዘርፉ ከተሰሩ አመርቂ ስራዎች መካከል ዋነኛ መሆኑ ነው የተብራራው።

በጤናው ዘርፍም በግዳጅ ላይ ለተጎዱ የሰራዊት አመራሮች እና አባላት ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በመነጋገር የተሻለ ህክምና እንዲያገኙ መደረጉን ያወሳው ሪፖርቱ ከሀገር ውስጥ የህክምና አገልግሎት በተጨማሪም በውጭ ሀገር የከፍተኛ ቀዶ ህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ስለመደረጉ ተጠቁሟል።

በመድረኩ የተገኙት በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የአስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያ ተወካይ እና የሰው ሃብት አስተዳደርና ልማት ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር አብዮት ሽፈራው እንደተናገሩት የአስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ተጨባጭ፣ ውጤታማ እና ተቋሙን አሻጋሪ የሆኑ ተግባራትን በስኬት አከናውኗል ብለዋል።

ረዳት ኮሚሽነር አብዮት ሽፈራው አክለውም ጠቅላይ መምሪያው በበጀት ዓመቱ ከክልል እስከ ዞን የዘለቀ የሰው ሃይል ግንባታና ምደባ፣ በተለያዩ ዘርፎች የስራ ላይ ስልጠና፣ የጂኦስትቴጂካዊ ስልጠናና ከኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ እና ከሌሎች የትምህርት ተቋማት ጋር በመነጋገር ከዲፕሎማ እስከ ሶስተኛ ድግሪ ድረስ ለበርካታ የፖሊስ አባላትና አመራሮች የትምህርት ዕድል መሰጠቱን ገልፀዋል።

የአስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያ የተቋሙ የጀርባ አጥንት ነው የሚሉት ረዳት ኮሚሽነር አብዮት ሽፈራው በተቋማዊ የሪፎርም ስራዎችና በሌሎች መደበኛ ተግባራት በኩል በበጀት ዓመቱ በርካታ ተግባራትን በስኬት ፈፅሟል ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ ከሰው ሀይል ግንባታ፣ ከሪፎርም አፈፃፀም፣ ከበጀት አስተዳደርና ሎጀስቲክ አጠቃቀም አንፃር በብዙ ችግሮች ውስጥ ሆኖ ተቋሙን የሚያሻግሩ ስራዎች ተሰርተዋል ነው ያሉት።

ረዳት ኮሚሽነሩ አያይዘውም በቀጣይ ፖሊስ ተቋሙን ተወዳዳሪ እና ተራማጅ ለማድረግ ለውጥ መር አስተሳሰብ ማምጣት፣ የአመራር ሚናን ለመወጣት የሚያስችል ብቃት መላበስ፣ የሪፎርም ስራዎችን አጠናክሮ የማስቀጠልና ስራን ቆጥሮ ሰጥቶ የመቀበል ልምድን ማዳበር፣ የሰራዊቱን ጥቅማ ጥቅም ማስከበር፣ የምልመላ ጥራትን ማስጠበቅ እንዲሁም ብቁ የሰው ኃይል መገንባት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ በትኩረት ከሚሰሩ የቀጣይ በጀት ዓመት አቅጣጫዎች መካከል ስለመሆናቸውም ተመላክቷል።

የመድረኩ ተሳታፊዎችም ጠቅላይ መምሪያው ስር ያሉ ሁሉም ዘርፎች ያከናወኗቸው ተግባራት ተቋሙን የሚያሳድጉ እና ለቀጣይ ተግባራት መነሻ የሚሆኑ መሆናቸውን ገልፀው የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ተቋሙን ብቁ፣ ተወዳዳሪና ስኬታማ ከማድረጋቸው ባሻገር ተቋማዊ ፍቅርና ክብር ያለው የፖሊስ ሰራዊት ለመገንባት የሚያስችሉ በመሆናቸው ሁሉም የፖሊስ ሰራዊት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top