“የ2018 ዓ.ም አፈጻጸም ስኬቶችን በማስፋት የህዝብን ደህንነት ማረጋገጥ ይገባል!” ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል አበበ ውቤ
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ስር የሚገኛው የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ በ2018 በጀት ዓመት ያከናወናቸውን አበይት የሰላምና የጸጥታ ማስከበር ተግባራት አፈጻጸም ገምግሟል።
በግምገማ መድረኩ ላይ በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ ዋና ዋና የጸጥታ፣ የህግ ማስከበር እና የትራፊክ ደህንነት ስራዎች በዝርዝር ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በዋናነትም በክልሉ ህገወጥ ታጣቂ ቡድኖችን በመቆጣጠር እና ህግን በማስከበር ረገድ በተደረገው መጠነ-ሰፊ እንቅስቃሴ የህዝብን ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት ማረጋገጥ መቻሉ በጠንካራ አፈጻጸምነት ተገምግሟል።
በተጨማሪም የመንግሥትም ሆነ የግል ተቋማት እንዲሁም መሰረተ-ልማቶች ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳይደርስባቸው የተካሄደው የጥበቃ ስራ እጅግ ውጤታማ እንደነበር ተነስቷል።
በዓመቱ ውስጥ በክልሉ የተካሄዱ በርካታ አበይት ሁነቶች ያለአንዳች የጸጥታ ስጋት በሰላም እንዲከወኑ መደረጉ በሪፖርቱ ተመላክቷል።
በተለይም 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ያለምንም የጸጥታ ችግር በሰላም እንዲጠናቀቅ የጸጥታ ኃይሉ ከሌሎች የጸጥታ እና የደህንነት ተቋማት ጋር ባደረገው የላቀ ቅንጅት የተከናወነው ተግባር ስኬታማ እንደነበር ተብራርቷል።
ህብረተሰቡን የሰላሙ ባለቤት ለማድረግ በማሰብ ክልል አቀፍ የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ (ኮሚዩኒቲ ፖሊሲንግ) አገልግሎት የንቅናቄ መድረክ በሁሉም የክልሉ ዞኖች መከናወኑ በግምገማው በጥንካሬ ከተነሱት ጉዳዮች ውስጥ ነው።
ከኢኮኖሚ አሻጥር ጋር በተያያዘም ህገወጥ የገንዘብ ዝውውርን እና የኮንትሮባንድ ንግድን በመቆጣጠር የተሰሩ ስራዎች በመልካም አፈጻጸም ላይ እንደሚገኙ ተመላክቷል።
ጠቅላይ መምሪያው በትራፊክ ደህንነት እና ቁጥጥር ዘርፍም የ2018 ዓ.ም አፈጻጸሙን የገመገመ ሲሆን፤ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ በተከናወኑ በርካታ እንቅስቃሴዎች አመርቂ ውጤት መመዝገቡ ተገልጿል።
የትራፊክ አደጋ በሚያጋጥምባቸው ቦታዎች የትራፊክ ፖሊስ አባላት ፈጥኖ በመድረስ የትራፊክ ፍሰቱ እንዳይስተጓጎል ለማድረግ የተከናወነው ተግባር እንዲሁም አጋዥ የተማሪ ትራፊክ አባላትን አሰልጥኖ ወደ ስራ በማስገባት በኩል የተመዘገበው ስኬት የተሻለ አፈጻጸም የታየባቸው ዘርፎች ናቸው።
ከዚህ ጎን ለጎን በሞተረኛ ትራፊክ ፖሊሶች የከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችን (VIP) ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ በማጀብ እና በማስተናበር በኩል እንዲሁም ነዳጅን ከተፈለገበት አላማ ውጭ የሚጠቀሙ አካላትን ስርዓት በማስያዝና ህገወጦችን በመቆጣጠር ረገድ የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡ ተጠቁሟል።
በግምገማ መድረኩ ላይ የተሳተፉ የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አመራሮች እና አባላት በበጀት ዓመቱ የተመዘገቡ ስኬቶችንና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን አስመልክቶ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የእቅድ አፈጻጸሙን አስመልክተው አስተያየት የሰጡት አመራሮች እንደገለጹት ህገወጥ የጦር መሳሪያና የኮንትሮባንድ ዝውውርን በመግታት ረገድ የተመዘገበው ውጤት ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው ይህም ሊሳካ የቻለው ህብረተሰቡ የጸጥታ ኃይሉን ደጋፊና መረጃ ሰጪ በመሆን አብሮ በመቆሙ እንደሆነ አረጋግጠዋል።
በተለይም የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ የንቅናቄ መድረኮች በየደረጃው መካሄዳቸው ፖሊስና ህዝብ በጋራ የወንጀል ስጋቶችን ቀድመው እንዲከላከሉ ትልቅ አቅም መፍጠሩን ገልጸዋል።
በትራፊክ ቁጥጥርና ደህንነት ዘርፍ የተሰማሩ የመንገድ ትራፊክ ቁጥጥር አመራሮች በበኩላቸው በትራፊክ አደጋ ቦታዎች ፈጥኖ በመድረስ በኩል የታየው መሻሻል የአሽከርካሪዎችንና የእግረኞችን እንግልት የቀነሰ መሆኑን ጠቁመዋል።
አጋዥ የተማሪ ትራፊክ አባላት ሰልጥነው ወደ ስራ መግባታቸው በትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚስተዋለውን የትራፊክ መጨናነቅና አደጋ በከፍተኛ ሁኔታ እንደቀነሰው የገለጹት አባላቱ ይህ ተሞክሮ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አመልክተዋል።
ተሳታፊዎቹ አያይዘውም ነዳጅን ከተፈለገበት ዓላማ ውጭ ለኮንትሮባንድና ለህገወጥ ተግባር የሚያውሉ አካላትን በቁጥጥር ስር ለማዋል የተደረገው ጥረት የህዝብን ጥቅም ያስጠበቀ እንደነበር ገልጸው በቀጣይም በግምገማው የተለዩ የንብረትና የሰው ኃይል ስምሪት ክፍተቶችን በማረም የተጀመረውን የሰላም ማስከበር ስራ አጠናክረው ለመቀጠል ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በግምገማ መድረኩ ላይ ተገኝተው የስራ መመሪያና የማጠቃለያ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል አበበ ውቤ በ2018 ዓ.ም የተመዘገቡት ስኬቶች የጸጥታ ኃይሉ ከህዝቡና ከሌሎች አቻ የጸጥታ አካላት ጋር ላደረገው የተቀናጀ ትግል ውጤት መሆናቸውን ገልጸዋል።
“የ2018 ዓ.ም አፈጻጸም ስኬቶችን በማስፋት የህዝብን ደህንነት ማረጋገጥ ይገባል!” ያሉት ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራሉ በቁርጠኝነት እና በቅንጅት ለዘላቂ ሰላምና የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ይገባል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራሉ በንግግራቸው ህገወጥ ታጣቂዎችን ከመቆጣጠር ጀምሮ የመንግስትንና የህዝብን ሃብት በመጠበቅ፣ እንዲሁም 7ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ጨምሮ በርካታ ሁነቶች በሰላም እንዲጠናቀቁ የክልላችን ፖሊስ ላሳየው ሙያዊ ጽናትና ቁርጠኝነት ምስጋና ይገባል ብለዋል።
ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራሉ አክለውም በትራፊክ ደህንነቱ፣ በኮንትሮባንድ ቁጥጥሩና በማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት የተመዘገቡትን አመርቂ ውጤቶች ይበልጥ በማስፋት እንዲሁም በግምገማው የታዩ ክፍተቶችን በፍጥነት በማረም በቀጣይም የህዝባችንን ደህንነት እና የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ አባሎቻችን በላቀ የፖሊሳዊ ስነ-ምግባር ሊተጉ ይገባል ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።












