“ዛሬ የምንተክለው እያንዳንዱ ችግኝ የነገዋን ውብና ሰላማዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት የምናስቀምጠው ዘላቂ አሻራ ነው” ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር)
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥና የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርን ለማሳካት ታስቦ የተዘጋጀውን የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር በዛሬው ዕለት በታላቅ ንቅናቄ አካሂዷል።
በዚሁ የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር ላይ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር)፣ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራሎች፣ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች እንዲሁም የጠቅላይ መምሪያው መደበኛና ሲቪል አባላት በነቂስ ተሳትፈዋል።
የችግኝ ተከላ ንቅናቄውን በይፋ ያስጀመሩት የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት ፖሊስ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ከመጠበቅ ባሻገር በሀገር ግንባታና በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎች ላይ ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆኑን በተግባር እያሳየ ይገኛል ብለዋል።
የአካባቢ መራቆትን መከላከልና የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም ከጸጥታና ደኅንነት ሥራችን ጋር ቀጥተኛ ትስስር አለው ያሉት ኮሚሽነር ጀኔራሉ “ዛሬ የምንተክለው እያንዳንዱ ችግኝ የነገዋን ውብና ሰላማዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት የምናስቀምጠው ዘላቂ አሻራ ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው አስገንዝበዋል።”
እንደ ኮሚሽነር ጀኔራሉ ገለጻ ፖሊሳዊ ግዴታችንን ከመወጣት ጎን ለጎን የተፈጥሮ ሚዛኑ የተጠበቀ አካባቢን ለትውልድ ማሻገር የሁላችንም የዜግነት ኃላፊነት ሊሆን ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር) አያይዘውም የተተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁና የታለመላቸውን ግብ እንዲያሳኩ ተከታታይ እንክብካቤ እንደሚደረግላቸው አረጋግጠዋል።
ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል ታደሰ አያሌው የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ እንደገለጹት ሰላም የመሬት ገጽታን ከአረንጓዴ ልማት ጋር ከማስተሳሰር ጭምር ይመነጫል ብለዋል።
ማኅበረሰቡን ያሳተፈ የጸጥታ ሥራችን ውጤታማ እንዲሆን ከተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ጋር ጎን ለጎን ማስኬድ ይገባናል ሲሉ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል ታደሰ አያሌው አስገንዝበዋል።
በመርሃ-ግብሩ ላይ የተሳተፉት ረዳት ኮሚሽነር አብዮት ሽፈራው በበኩላቸው የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በጠቅላይ መምሪያው አባላት ዘንድ ከፍተኛ መነሳሳት የተታየበት መሆኑን ገልጸዋል።
ዛሬ በሰፊው ያካሄድነው የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር ተቋማዊ ገጽታችንን ከመገንባት ባለፈ ለአባላቶቻችን ምቹ የሥራ አካባቢን ለመፍጠር ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
በችግኝ ተከላው ላይ በንቃት የተሳተፉ የዋና ጠቅላይ መምሪያው ከፍተኛ የፖሊስ አመራሮችና አባላትም የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
አስተያየታቸውን የሰጡ አባላት እንደተናገሩት በችግኝ ተከላ መርሃ-ግብሩ ላይ መሳተፋቸው ለአረንጓዴ ልማት ያላቸውን ተቆርቋሪነት የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ የተተከሉትን ችግኞች ተንከባክቦ ማሳደግ ላይ የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
እኛ የፖሊስ አባላት ሕዝባችንን ከወንጀልና ከጸጥታ ስጋት እንደምንጠብቀው ሁሉ ይሄንን የአረንጓዴ አሻራ ልማትም የነገ ሕይወታችን ዋስትና መሆኑን ተገንዝበን በቁርጠኝነት እንንከባከባለን ሲሉ አባላቱ ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ባካሄደው በዚህ መርሃ-ግብር በአካባቢው ጥናት የተደረገባቸውና ለቦታው ተስማሚ የሆኑ ልዩ ልዩ ችግኞች መተከላቸው ታውቋል።








