“የደምብ ልብሱ የፖሊስን ተቋማዊ ሪፎርም እና ዝግጁነት የሚያሳይ ነው!!” ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር)
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ወቅቱንና ጥራቱን የጠበቀ አዲስ የሰራዊት ደምብ ልብስ አስተዋወቀ።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የፖሊስ ሰራዊቱን አቅም ለመገንባትና ተቋማዊ ሪፎርሙን ለማፋጠን ካከናወናቸው አንኳር ተግባራት መካከል የሰራዊቱን ክብርና ሞገስ የሚመጥን፣ ጥራቱን የጠበቀ እና ወቅቱን የዋጀ የደምብ ልብስ ማቅረብ መሆኑ ተገለጿል።
ይህንኑ ተከትሎ ዛሬ በዋና መስሪያ ቤቱ አዲስ የተዘጋጀው የፖሊስ ደምብ ልብስ (ዩኒፎርም) ይፋዊ የትውውቅ መርሃ ግብር ተካሂዷል።
በዚሁ የትውውቅ ስነ-ስርዓት ላይ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር)፣ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራሎች፣ የዋና መስሪያ ቤቱ ስትራቴጅክ እና ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የአባላት ተገኝተዋል።
በዕለቱ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ፖሊስ የህዝብን ሰላምና ደህንነት የማስከበር ከባድ ኃለላፊነቱን በብቃት ለመወጣት ተቋማዊ ቁመናውን ማዘመን እንደሚገባው ገልጸዋል።
“የደምብ ልብሱ የፖሊስን ተቋማዊ ሪፎርም እና ዝግጁነት የሚያሳይ ነው!” ያሉት ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ይህ አዲስ የደምብ ልብስ ሰራዊቱ በዓይነት፣ በጥራትና በመጠን ተደራሽ እንዲሆን ተደርጎ የተዘጋጀ ነው ሲሉ አክለዋል።
የደምብ ልብሱ ወቅቱን የዋጀና የፖሊስን ሙያዊ ክብር የሚያጎላ በመሆኑ ሰራዊቱ ያለበትን የሰላም ማስከበርና የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ግዳጅ ይበልጥ በልበ-ሙሉነትና በትጋት ለመወጣት ትልቅ መነቃቃትን ይፈጥራል ብለዋል።
ኮሚሽነር ጀኔራሉ አክለውም የሰራዊቱን ሁለንተናዊ ፍላጎት በማሟላት ረገድ የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
የዕለቱን ዝግጅት አስመልክቶ ሀሳባቸውን የሰጡት ረዳት ኮሚሽነር አብዮት ሽፈራው የአስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ተወካይ በበኩላቸው የደምብ ልብስ አቅርቦት ለአንድ የጸጥታ መዋቅር ካለው ስልታዊ ጠቀሜታ አንጻር ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት የተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
አዲሱ የደምብ ልብስ የክልሉን ፖሊስ ወደ ቀደመ ክብሩና ዝናው ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ትልቅ እርምጃ ነው ሲሉ ረዳት ኮሚሽነር አብዮት አክለዋል።
አዲሱ የደምብ ልብስ ደረጃውን የጠበቀ እና ለስራ ምቹ ሆኖ መዘጋጀቱን በመግለጽ ይህም የሰራዊቱን ስነ-ምግባርና ዝግጁነት ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው እና ለተግባራዊነቱም አመራሩ አስፈላጊውን ክትትል ድጋፍ እንደሚያደርግ ረዳት ኮሚሽነር አብዮት ሽፈራው አስገንዝበዋል።
በትውውቅ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የፖሊስ አመራር እና አባላት በሰጡት አስተያየት አዲሱ የደምብ ልብስ ወቅቱን የዋጀ፣ ጥራቱ የተረጋገጠ እና በመጠን ደረጃም ለአባላቱ ምቹ ሆኖ መቅረቡን በደስታ እንደሚቀበሉት ገልጸዋል።
ይህ አይነቱ የተሟላ አቅርቦት ለሙያቸው ያላቸውን ክብር እንደሚያሳድገውና የተጣለባቸውን የህዝብ አደራና የሰላም ጥበቃ ተልዕኮ በላቀ ተነሳሽነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን በቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
ይህ አዲስ የደምብ ልብስ አቅርቦት የክልሉ ፖሊስ ራሱን በዕውቀት፣ በስነ-ምግባርና በትጥቅ በማደራጀት የህዝብን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ለጀመረው ጉዞ ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን ተመልክቷል።















