“በኋላቀር አሰራርና በድሮ ገጽታ የምንቀጥልበት ዘመን የለም!” ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር)

“በኋላቀር አሰራርና በድሮ ገጽታ የምንቀጥልበት ዘመን የለም!” ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር)

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ እና በጎንደር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ የተጠናቀቁና በመከናወን ላይ ያሉ የተቋማዊ ሪፎርም ስራዎችንና የቢሮ ዕድሳት ፕሮጀክቶችን ጎበኙ።

ኮሚሽነር ጀኔራሉ በጉብኝታቸው የተገኙትን ለውጦች በማድነቅ የቀጣይ የስራ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል።

ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ በተገኙበት ወቅት በተቋሙ የተከናወነውን ስር-ነቀል የቢሮ ዕድሳትና የተቋሙን ገጽታ ለማዘመን የተደረጉ ስራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

መምሪያው በአጭር ጊዜ ያሳካው የገጽታና የስራ አካባቢ ለውጥ የሚያኮራና ለሌሎች ተቋማትም በምሳሌነት የሚጠቀስ ተሞክሮ መሆኑን ገልጸው ለስራው መሳካት ሌሊትና ቀን ለደከሙ የስራ ኃላፊዎችና አባላት አበረታች መልዕክት አስተላልፈዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ እያካሄደ ያለው ተቋማዊ ሪፎርም አንዱና ዋና ዓላማ ዘመናዊ፣ ምቹ፣ ጽዱና ቀልጣፋ የስራ አካባቢ በመፍጠር ለፖሊስ አባላት ከፍተኛ የስራ ተነሳሽነትን መፍጠርና ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት ማዘመን መሆኑን ኮሚሽነር ጀኔራሉ ገልጸዋል።

እንደ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ገለጻ “በኋላቀር አሰራር እና በድሮ ገጽታ የምንቀጥልበት ዘመን የለም!” በማለት አጽንኦት ሰጥተው አብራርተዋል።

ኮሚሽነር ጀኔራሉ አክለውም ተቋሙ ከዘመኑ ጋር የሚራመድ፣ በዘመናዊ አሰራርና ቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው ይህ የሪፎርም ስራ የአማራ ክልል ፖሊስን ከአሮጌ አሰራር በማላቀቅ ዓለም አቀፍ የፖሊስ ተቋማት ደረጃ ላይ ለማድረስ ያለመ መሆኑን አስታውቀዋል።

የፖሊስ መምሪያው ለረጅም ዓመታት ከፖሊስ ተቋም ክብርና ስም ጋር የማይመጣጠን ገጽታ ይዞ መቆየቱን አስታውሰው ዛሬ የተፈጠረው አዲስ ተቋማዊ ቁመና ለሰራዊቱ ትልቅ ኩራትና የሞራል ስንቅ እንደሚሆን አብራርተዋል።

ለታደሱት ቢሮዎች የሚመጥኑ ዘመናዊ የቢሮ ቁሳቁሶች፣ የአይሲቲ (ICT) መሳሪያዎችና ሌሎች አስፈላጊ ማቴሪያሎች ደረጃ በደረጃ እንዲሟሉ አቅጣጫ የሰጡት ዋና አዛዡ፤ ከዘመኑ ጋር አብሮ መራመድ ምርጫ ሳይሆን የሕልውና ጉዳይ መሆኑን እና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ቀልጣፋ አገልግሎት ለህዝብ መስጠት የሪፎርሙ ዋና ማዕከል መሆኑን አስገንዝበዋል።

በተመሳሳይ ዜና ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ በጎንደር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ በመከናወን ላይ ያለውን የቢሮ ዕድሳት ሂደት ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

በጉብኝት መርሃ-ግብሩ ላይ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ ደብሬ የሗላ፣ የቀድሞ የፖሊስ አባላት፣ በጡረታ የተገለሉ የሀገር ባለውለታዎች እና የከተማዋ የሀገር ሽማግሌዎች በመገኘት ለኮሚሽነር ጀኔራሉ ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

የፖሊስ ተቋም ከህብረተሰቡ፣ ከአካባቢው አመራሮችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅትና በባለቤትነት ስሜት ሲሰራ ለጎንደር ከተማና ለአካባቢው ተጨማሪ ውበት፣ ኩራትና የተሻለ የስራ ባህል መፍጠር እንደሚቻል በጉብኝቱ ወቅት ተገልጿል።

በመጨረሻም ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ለዕድሳት ስራዎቹ ስኬት የጎንደር ከተማ አስተዳደር ላሳየው ከፍተኛ ትብብርና ቁርጠኝነት ምስጋናቸውን አቅርበው፤ የዕድሳት ኮሚቴዎችና በሂደቱ የተሳተፉ አካላት በሙሉ ያበረከቱትን የላቀ አስተዋጽኦ በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ስም አድንቀዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top