ባጃጅ ውስጥ ከለውዝ ጋር ተደብቆ ሲጓጓዝ የነበረ ከ5 ሺህ በላይ የክላሽ ጥይት በቁጥጥር ስር ዋለ።

ባጃጅ ውስጥ ከለውዝ ጋር ተደብቆ ሲጓጓዝ የነበረ ከ5 ሺህ በላይ የክላሽ ጥይት በቁጥጥር ስር ዋለ።

በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የፈንድቃ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ከሰዋታፕ ወደ ፈንድቃ ከተማ በሕገ-ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበረ 5 ሺህ 28 የክላሽ ኮቭ ተተኳሽ ጥይት መያዙን አስታወቀ።

የፈንድቃ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር አደራጀው አሰፋ እንደገለጹት ሕገ-ወጥ ጥይቱ የተያዘው ከለውዝ ጋር ተቀላቅሎ በባጃጅ ተሽከርካሪ ውስጥ በምስጢር ሲጓጓዝ በነበረበት ወቅት ነው።

የጸጥታ አካላት በኬላ ላይ ባደረጉት ጥብቅ ፍተሻና የጋራ ቅንጅት (በጥምር ጦሩ) አማካኝነት ይኸው ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ጥይት ሊያዝ መቻሉን ኃላፊው አረጋግጠዋል።

ምክትል ኢንስፔክተር አደራጀው አሰፋ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ባስተላለፉት መልእክት ሕገ-ወጥ ተግባራት የአካባቢው የጸጥታ ችግርና አለመረጋጋት ምንጭ በመሆናቸው ኅብረተሰቡ እንዲህ ያሉ ድርጊቶችን ቀድሞ በመጠቆምና በመከላከል ረገድ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር ያለውን ትብብር ማጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል።

የአካባቢያችንን ሰላምና ደህንነት ዘላቂ ለማድረግ የሰፈር ሮንድ ጥበቃን ማጠናከር፣ ጸጉረ-ለውጥ (አጠራጣሪ) ሰዎችን ለሕግ አካላት መጠቆምና ከጸጥታ ኃይሎች ጋር በቅንጅት መሥራት ወሳኝ ነው ሲሉ ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል።

በአሁኑ ወቅት በጉዳዩ ላይ ፖሊስ ጥብቅ ምርመራ እያደረገ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top