የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዋና መምሪያ የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈፃፀሙን ገመገመ

የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዋና መምሪያ የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈፃፀሙን ገመገመ

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዋና መምሪያ የ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት የሥራ አፈፃፀም ግምገማውን አካሂዷል።

መምሪያው በበጀት ዓመቱ ውስጥ የነበሩትን ጠንካራና ደካማ ጎኖች በዝርዝር የገመገመ ሲሆን፣ በተለይም ፖሊስንና ሕዝብን በማስተሳሰር ረገድ ከፍተኛ ስኬት መመዝገቡን አመልክቷል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ እንደገለጹት፤ በበጀት ዓመቱ ዋና መምሪያው ከፈፀማቸው በርካታ ተግባራት መካከል የፖሊስና የሕዝብን ትስስር በማጠናከር፣ ለሕብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር ወንጀልን አስቀድሞ በመከላከል ረገድ አመርቂ ተግባራት መከናወናቸውን ገልፀዋል።

የተቋሙን የለውጥ፣ መደበኛና የሕግ ማስከበር ሥራዎች ለሕዝብና ለሰራዊቱ ተደራሽ በማድረግ ረገድ የዋና መምሪያው የሚዲያ ክፍል ወቅታዊ፣ ተዓማኒና አስተማሪ የሆኑ መረጃዎችን በፍጥነት በማድረስ እጅግ ንቁና ተፅዕኖ ፈጣሪ ተሳትፎ ማድረጉንም ገልፀዋል ።

ዋና መምሪያው መረጃን ለሕዝብ ከማድረስ ባለፈ በፖሊስና በማኅበረሰቡ መካከል ጠንካራ ድልድይ በመሆን የጋራ መተማመንን በመፍጠር፣ ወንጀሎች ሳይፈጸሙ በፊት በማኅበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት እቅድ አማካኝነት አስቀድሞ የመከላከል አቅምን በማሳደግና የተሳሳቱ መረጃዎችን በወቅታዊና ትክክክለኛ መረጃ በመቀየር የክልሉን ሰላምና ጸጥታ የማረጋገጥ ከፍተኛ ሚና እንደተወጣም ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ ጠቁመዋል።

በማርች ባንድ፣ በሙዚቃናቲያትር እንዲሁም በስፖርት ክፍሎች በኩል በውጤት የታጀቡ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን የገለጹት ኃላፊው፣ የስራ ቦታ ማስዋብና የሙያ ስልጠናዎችን የመስጠት ተግባራትም በበጎ ጎናቸው የተጠቀሱ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዋና መምሪያ ለሁሉም የፖሊስ አደረጃጀቶች አርአያ በመሆኑ የተሰጠውን መንግስታዊ ኅላፊነት በአግባቡ በመወጣት ለህዝብ ሰላም፣ልማትና መልካም አስተዳደር መስፈን በቁርጠኝነት፣በትጋትና በትኩረት ሊሰራ ይገባል ሲሉም ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በግምገማ መድረኩ ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የተቋማዊ ለውጥ ሥራዎች መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ነጋ ድንበሩ በበኩላቸው፤ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዋና መምሪያ የተከናወኑ ተግባራት ፖሊስ ተቋሙን ከማኅበረሰቡ ጋር በመስተሳሰርና ተቋሙ እየፈፀማቸው ያሉትን መደበኛና የሕግ ማስከበር ሥራዎች ተደራሽ በማድረግ ረገድ የአንበሳውን ድርሻ ተወጥቷል ሲሉ ተናግረዋል።

ኮማንደር ነጋ አክለውም፣ ተቋሙ አሁን ላይ ያለውን ተጨባጭና ውስብስብ የጸጥታ ችግር በጽናት በመቋቋም ሕዝባዊና ተቋማዊ ግዴታውን በብቃት እየተወጣ እንደሚገኝና ከተለመደው አሠራር ወጥቶ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር ረገድ የተደረገው ጥረት ውጤታማና የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ የተሰሩ ሥራዎች ውጤታማ፣ ተጨባጭና ለቀጣይ ሥራዎች ተነሳሽነትን የሚጭሩ መሆናቸውን ጠቁመው፣ በልዩ ልዩ ሁኔታ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በመቅረፍ በቀጣይ በጀት ዓመት የበለጠ ውጤታማ ሥራ መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

የሚዲያና ሕዝብ ግንኙነት ሥራ ለአንድ የጸጥታ ተቋም ተራ መረጃ ማስተላለፊያ ሳይሆን የተቋሙ የጀርባ አጥንትና የልብ ትርታ መሆኑንም አፅንኦት ሰጥተውታል።

አመታዊ የስራ ክንውኑ ተቋሙ ያለበትን ተለዋዋጭ የሰላምና ደህንነት ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገባ፣ የውስጥ አቅምንና ሪሶርስን በአግባቡ የተጠቀመ እንዲሁም በውጤት ደረጃም ተጨባጭ ለውጥ ያመጣ መሆኑን በግልጽ ያሳያል ብለዋል።

ተቋሙ የጀመረው የለውጥና የሪፎርም ሥራ ውጤታማ መሆኑን የጠቆሙት ተሳታፊዎቹ ሪፎርሙ በተቋሙ ውስጥ የሥራ ባህልን በማጠናከር፣ የአገልግሎት ጥራትን በማሻሻልና ሠራተኞች የተሻለ የሥራ መነሳሳትና ተሳትፎ እንዲኖራቸው አዎንታዊ ሚና መጫወቱን አስረድተዋል።

በመጨረሻም ዋና መምሪያው በበጀት ዓመቱ የታዩ ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠልና ያጋጠሙ ማነቆዎችን በመቅረፍ፣ በቀጣይም የአሰራር ስትራቴጂውን ይበልጥ በማዘመንና ዘርፉን ይበልጥ በማጠናከር የክልሉን ሰላምና ደኅንነት የማስከበር ተልዕኮውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተመላክቷል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top