በአፋር እና በአማራ አዋሳኝ አካባቢዎች ሰላምን ለማፅናት ያለመ የውይይት መድረክ መጀመሩ ተገለፀ።

በአፋር እና በአማራ አዋሳኝ አካባቢዎች ሰላምን ለማፅናት ያለመ የውይይት መድረክ መጀመሩ ተገለፀ።

በአፋር እና በአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እና የሁለቱን ተጎራባች ማህበረሰቦች የጋራ ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማሳደግ ያለመ የህዝብ ለህዝብ የውይይት መድረክ መካሄድ ጀምሯል።

አቶ ቸሩ ጌታ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ፣ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ፣ ዶ/ር እሸቱ የሱፍ የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ እና በቀጠናው የተሰማሩ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አመራሮች፣ የሁለቱ ክልሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የጸጥታ አካላት፣ የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የሃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።

በአሁኑ ወቅት በአዋሳኝ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የጸጥታ ስጋቶችን በዘላቂነት መፍታት በሚቻልባቸው አማራጮች ላይ ሰፊ ውይይት እየተደረገ ይገኛል።

የዚህ መድረክ መካሄድ በአካባቢው አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን የጸጥታ አካላት እና ህብረተሰቡ በቅንጅት የሚሰሩበትን አቅጣጫ ከማስቀመጥ ባለፈ የሁለቱን ክልሎች ህዝቦች ታሪካዊና ባህላዊ ትስስር መሰረት በማድረግ የንግድና ማህበራዊ ግንኙነቶችን ማጠናከር ላይ ያለመ ነው።

ሰላምን የሚያደፈርሱ የኮንትሮባንድ፣ የህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር እና ሌሎች የወንጀል ድርጊቶችን በጋራ ለመግታት መስማማት፤

በአንድ ክልል ላይ ወንጀል ፈፅመው ፍትህን በመሸሽ ወደ አማራ ወይም ወደ አፋር ክልል የሚሻገሩ ወንጀለኞችን ክትትል በማድረግ፣ ተፈላጊዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ አሳልፎ የመስጠት ቁርጠኝነት፤

በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ እና የህዝቡን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ የጽንፈኝነት ኃይሎችን እንቅስቃሴ በጋራ የመቆጣጠር፣ የመከላከልና የማክሸፍ ስራዎችን ማከናወን፤ በሚሉ ከፖሊስና ከጸጥታ ስራ አንጻር ወሳኝ ስምምነቶች ላይ ያተኩራል ተብሎ ይጠበቃል።

ሁለቱ ተጎራባች ማህበረሰቦች ለዘመናት በሰላምና በፍቅር አብረው የኖሩ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ይህ መድረክ የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እና ዘላቂ የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ተመላክቷል።

የሁለቱም ክልሎች የጸጥታ አካላት በመድረኩ የተደረሱትን ስምምነቶች በተግባር ለመተርጎም፣ የወንጀል መከላከል ስራውን በቅንጅት ለመምራትና የአካባቢውን ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ ሙሉ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top