እናንተ ከአማራ ክልል ፖሊስ ባሻገር የሀገራችን ኢትዮጵያ አምባሳደሮች ናችሁ!! ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር)
በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) የተመራ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ቡድን በደብረ ብርሃን ከተማ በመገኘት ከአማራ ክልል ፖሊስ አትሌቲክስ ክለብ አባላት፣ አሰልጣኞችና የቡድን መሪዎች ጋር ሰፊና ሁሉን አቀፍ ውይይት አካሂደዋል።
በመድረኩ ላይ የክልሉ ፖሊስ ኮሙኒኬሽን እና ህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ፣ የሰሜን ሸዋ ዞን እና የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያዎች የማኔጅመንት አባላት እንዲሁም የክለቡ አመራርና ስፖርተኞች ተገኝተዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) በውይይቱ ወቅት ባደረጉት ንግግር የአትሌቲክስ ቡድኑ አባላት የሚጠበቅባቸውን ክልላዊ ግዳጅ ከመወጣት ባለፈ በስፖርቱ መስክ የሚያስመዘግቡት ስኬት ትልቅ ትርጉም እንዳለው ገልጸዋል።
“እናንተ ከአማራ ክልል ፖሊስ ባሻገር የሀገራችን ኢትዮጵያ አምባሳደሮች ናችሁ!!” ያሉት ኮሚሽነር ጀኔራሉ ተቋሙ የአማራ ክልል ፖሊስ አትሌቲክስ ክለብን ዘመኑን የሚመጥን፣ በንቃተ ህሊና እና በስነ-ምግባር የታነጸ ዘመናዊ ቡድን ለማድረግ በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።
ተቋሙ በስፖርቱ ዘርፍ የጀመረው ሁሉን አቀፍ ሪፎርም ውጤት እያመጣ መሆኑን የጠቀሱት የፖሊስ አዛዡ በተለይም በአሰልጣኝ እና የቡድን መሪዎች አመዳደብ ላይ ‘ሙያ እና ሙያተኛን ያገናኘ’ አሰራር መዘርጋቱ ለክለቡ ፈጣን እድገትና ጥንካሬ መሰረት መጣሉን አስገንዝበዋል።
የኮሙኒኬሽን እና ህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ በበኩላቸው ባስተላለፉት መልዕክት ቀደም ሲል ተበትኖ የነበረውን የአትሌቲክስ ክለብ እንደገና በማሰባሰብ፣ መዋቅራዊ ቅርፅ እንዲይዝና ውጤታማ እንዲሆን ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ላደረጉት ቀጥተኛ አመራርና ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
ይህ ድጋፍ ስፖርቱን ብቻ ሳይሆን የተቋሙን መልካም ገጽታ የሚገነባውን የኮሙኒኬሽን እና ህዝብ ግንኙነት ስራን በከፍተኛ ደረጃ የሚያጠናክር መሆኑን ረዳት ኮሚሽነሩ አብራርተዋል።
በተቋሙ በኩል እየተደረገ ያለው ከፍተኛና ተከታታይነት ያለው ድጋፍ ክለቡን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ስኬት ማማ እንዳሸጋገረው የአትሌቲክስ ቡድኑ አመራሮች እና አባላት በመድረኩ ገልጸዋል።
ለዚህም ማረጋገጫ የሚሆነው ክለቡ በቅርቡ በተካሄዱ ውድድሮች ከተዘጋጁ 5 የሻምፒዮና ዋንጫዎች መካከል 3ቱን በበላይነት በማንሳት የአማራ ክልል ፖሊስን ስም ማስጠራት መቻሉ ነው ሲሉ አክለዋል።
በውይይቱ ወቅት የክለቡ አትሌቶችና አሰልጣኞች ባነሷቸው ሃሳቦች ተቋሙ እያደረገላቸው ላለው ድጋፍና ለተሰጣቸው ሙያዊ እውቅና ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በቀጣይም ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን የሚያስችሉ የቁሳቁስ፣ የልምምድ ቦታዎች ምቾት እና የረጅም ጊዜ ዝግጅት ማዕቀፎችን የተመለከቱ ጥያቄዎችንና ሃሳቦችን ሰንዝረዋል።
ከስፖርተኞቹ ለተነሱት ሃሳቦችና ጥያቄዎች የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ዝርዝር ምላሽና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን በቀጣይም ክለቡን ይበልጥ ለማዘመን የሚረዱ የሚከተሉት ዋና ዋና የስራ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል።
በሳይንሳዊ እና ዘመናዊ የአሰልጣኝነት ጥበብ ላይ የተመሰረተ ስልጠና ለስፖርተኞችና ለአሰልጣኞች መስጠትን አጠናክሮ መቀጠል፤
የክለቡን የስልጠና ቁሳቁስ፣ የተመጣጠነ ምግብ እና የህክምና አገልግሎት ደረጃን በየጊዜው በማሻሻል አትሌቶች ሙሉ ትኩረታቸውን በውጤት ላይ ብቻ እንዲያደርጉ ማስቻል፤
የሰሜን ሸዋ ዞን እና የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያዎች ለክለቡ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ የሚያደርጉበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር፤
በሃገር አቀፍና በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የክልሉን ፖሊስና የሀገርን ሰንደቅ አላማ ከፍ የሚያደርጉ አትሌቶችን የማፍራት ስራን በዕቅድ መምራት መሆናቸውን አጽንኦት ሰጥተው አብራርተዋል።
በማጠቃለያውም የስፖርት ቡድኑ አባላት የተጣለባቸውን ክልላዊና ሀገራዊ አምባሳደርነት ሚና በተግባር ለማረጋገጥና የጀመሩትን የድል ጉዞ አጠናክረው ለመቀጠል ቃል ገብተዋል።
በመጨረሻም የአትሌቲክስ ክለቡ በቅርቡ በተደረጉ ውድድሮች ያገኛቸውን ዋንጫዎች ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) በክብር አስረክበዋል።















