“ለጀግኖቻችን ብቁ ማዕከል ለመገንባት ሌት ተቀን እየሰራን ነው!!” ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር)
በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ እየተገነባ የሚገኘው የጀግኖች ማዕከል ግንባታ ‘ለሰራዊቱ በሰራዊቱ’ በሚል ታላቅ መርህ እውን እየሆነ ይገኛል።
ይህ ታላቅ ፕሮጀክት እየተገነባ የሚገኘው የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ በኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ካሳተሙት መጽሐፍ ሽያጭ በተገኘ ገቢ እና መላው የፖሊስ ሰራዊት አባላት ካደረጉት መዋጮ ነው። ማዕከሉ በራሱ አቅም ታሪክን ለመዘከርና ሰራዊቱን ለመንከባከብ የተጀመረ የቁርጠኝነት እና የህብረት ደማቅ ማሳያ ነው።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) እየተገነባ የሚገኘውን የጀግኖች ማዕከል የግንባታ ሂደት በአካል ተገኝተው የመስክ ጉብኝት አካሂደዋል።
ኮሚሽነር ጀኔራሉ በጉብኝታቸው ወቅት እንዳሉት የማዕከሉ ግንባታ በአሁኑ ወቅት በጥሩ ሒደትና ደረጃ ላይ ይገኛል። ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ተጠናቆ ለአገልግሎት ሲበቃ የፖሊስ ሰራዊቱን አቅም፣ ዝግጁነትና ሞራል ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ የሚያደርግና ለሰራዊቱ ትልቅ አቅም የሚሆን ተቋም መሆኑን ገልጸዋል።
“ለጀግኖቻችን ብቁ ማዕከል ለመገንባት ሌት ተቀን እየሰራን ነው!” ያሉት ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) የጀግኖች ማዕከል ግንባታ ሲጠናቀቅ ለሰራዊታችን ሁለንተናዊ አቅም የሚገነባ ትልቅ ተቋም ይሆናል ሲሉ አክለዋል።
የጀግኖች ማዕከል ግንባታ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ያስታወቁት ኮሚሽነር ጀኔራሉ ይህ ፕሮጀክት የሰራዊቱን ወትሮ ዝግጁነት እና ቁርጠኝነት በላቀ ደረጃ ለማሳደግ ሚናው የጎላ ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው አብራርተዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና አዛዡ አክለውም ግንባታው በተቀመጠለት ጥራትና የጊዜ ሰሌዳ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ የዋና ጠቅላይ መምሪያው አመራርና የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
በሳይቱ ላይ የሚገኙ የኮንስትራክሽን ባለሙያዎች በበኩላቸው የግንባታ ስራው ደረጃውንና ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን ሌት ተቀን እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለሙያዎቹ የጀግኖች ማዕከል መገንባት ያለውን ታሪካዊና ሙያዊ ፋይዳ በሚገባ እንረዳለን፤ ስለሆነም የተጣለብንን ኃላፊነት በታማኝነትና በከፍተኛ ሙያዊ ስነ-ምግባር በመወጣት ግንባታውን በተቀመጠው ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተጋን ነው ሲሉ አስረድተዋል።
በጉብኝቱ ላይ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የአትሌቲክስ ቡድን አባላትና አመራሮችም የተሳተፉ ሲሆን ማዕከሉ ለስፖርተኞችና ለጠቅላላው ሰራዊት የሚኖረውን ጠቀሜታ አጉልተዋል።
የአመራርና የአትሌቲክስ ቡድኑ አባላት በሰጡት አስተያየት ይህ የጀግኖች ማዕከል ግንባታ መጀመሩና በዚህ ደረጃ ላይ መድረሱ ለኛ ለስፖርተኞችና ለአጠቃላይ ሰራዊቱ ትልቅ ኩራትና መነሳሳት ነው ብለዋል።
ማዕከሉ አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ብቃታችንን ለማሳደግ እና ውጤታማነታችንን ለማስቀጠል ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል በማለት ግንባታው በፍጥነት እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
ይህ የጀግኖች ማዕከል ግንባታ መጠናቀቅ የክልሉን ፖሊስ የውስጥ አቅም በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሳድገውና ለሰራዊቱ ሁለንተናዊ ዝግጁነት ስትራቴጂካዊ ፋይዳ እንዳለው በጉብኝቱ ወቅት ተመላክቷል።
በጉብኝታቸው ማጠቃለያም ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) በደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ የከተማዋን የፖሊስ አገልግሎት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እየተገነባ የሚገኘውን አዲስ የቢሮ ግንባታ ሂደት በአካል ተገኝተው ተመልክተዋል። ይህ የቢሮ ግንባታ የፖሊስ ተቋማትን ለማዘመንና ለሰራዊቱ ምቹ የስራ አካባቢ ለመፍጠር እየተደረገ ካለው ሰፊ ጥረት አንዱ አካል ነው።









