የጸጥታ ኃይሉ የሕዝብን ሰላምና የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር ታሪካዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑ ተገለጸ።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ስትራቴጂክ አመራሮች በተገኙበት የሰሜን ወሎ ዞን እና የወልድያ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የአድማ መከላከል ፖሊስ 24ኛ ሻለቃ የግዳጅ አፈጻጸምና የተቋም ሪፎርም ግምገማ ክልል አቀፍ የውይይት መድረክ በወልድያ ከተማ ተካሂዷል።
በከፍተኛ የፖሊስ አመራሮች በተመራው በዚህ መድረክ ላይ የተከናወኑ ተግባራት በጥልቀት የተገመገሙ ሲሆን፣ የጸጥታ ኃይሉ የሕዝብን ደኅንነት ለማረጋገጥ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አራጌ ይመር ባደረጉት ንግግር ባለፉት ሦስት ዓመታት በክልሉና በዞኑ ያጋጠሙ የጸጥታ ችግሮችን ለመቀልበስና የሀገር ማፍረስ ሴራዎችን ለማክሸፍ የፖሊስና የአድማ መከላከል አመራሮችና አባላት ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመሆን የአንበሳውን ድርሻ መወጣታቸውንና ውድ መሥዋዕትነት መክፈላቸውን ገልጸዋል።
ለመድረኩ የመነሻ ሐሳብ ያቀረቡት የአብክመ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር አበበ ውቤ በዞኑ አስተማማኝ የጸጥታ መሻሻል ለመታየቱ ዋናው ማሳያ ኅብረተሰቡ ከጸጥታ ኃይሉ ጎን መሰለፉና የዘንድሮው 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ፍጹም ሰላማዊ ሆኖ መጠናቀቁ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም ክልሉን ፍጹም ሰላማዊ በማድረግ የልማትና ራስን የማስተዳደር ዕቅዶችን ለማሳካት አባላቱ የተጣለባቸውን ግዳጅ በጀግንነት እንደሚወጡ ሙሉ እምነት እንዳላቸው አረጋግጠዋል።
እንደ ኮሚሽነሩ ማብራሪያ የተሰጡ ግዳጆች የተፈጸሙበትን ደረጃ በጥልቀት መገምገም፣ የተካሄደው የተቋም ሪፎርም ያመጣውን መዋቅራዊና አሠራራዊ የለውጥ ውጤታማነት መፈተሽ 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የተደረገውን የተቀናጀ ጥረት ጠቃሚ ተሞክሮዎችን በቀጣይ ሥራዎች ላይ ማደራጀት እንዲሁም በጸጥታ ኃይሉ፣ በፖለቲካ አመራሩና በኅብረተሰቡ መካከል ያለውን የጋራ ቅንጅት ይበልጥ ማጠናከር የውይይቱ ዋነኛ ዓላማዎች ናቸው።
የሰሜን ወሎ ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ፈንታ ተጋፋው በበኩላቸው የፖሊስ አባላት ለሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ሲሉ ያሳዩት ጽናት፣ የከፈሉት መሥዋዕትነትና የተሰጣቸውን ግዳጅ በብቃት የመወጣት አቅማቸው እጅግ የሚያስመሰግን መሆኑን ገልጸዋል። ይህ አባላቱ እያሳዩት ያለው ተቋማዊ ታማኝነትና የሕዝብ ወገንተኝነት በቀጣይ ለሚከናወኑ የሕግ ማስከበርና የሰላም ግንባታ ሥራዎች ትልቅ ጉልበት የሚሰጥ መሆኑንም አክለዋል።
በመድረኩ ላይ የአብክመ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው እና የሰው ኃይል አስተዳደርና ልማት ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር አብዮት ሽፈራውን ጨምሮ በርካታ የአመራር አካላትና የአድማ መከላከል ፖሊስ አባላት ተገኝተዋል።
በማጠቃለያውም መድረኩ በጸጥታ ኃይሉና በአመራሩ መካከል ጠንካራ የጋራ መግባባትን የፈጠረ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ የውይይቱ ተሳታፊዎች በቀጣይ የሚሰጡ ማናቸውንም ተልእኮዎችና ግዳጆች እጅ ለእጅ ተያይዘው ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመወጣት ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል።







