“የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ማክበር ዋነኛ መርዓችን ነው!” ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር
የአለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ (ICRC) የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ልዑካን ቡድን ከአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ጋር በሰብዓዊ መብት አጠባበቅ፣ በሙያዊ ስልጠናዎች እና ተያያዥ በሆኑ የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ በትብብር ለመስራት የሚያስችል ፍሬያማ ውይይት አካሄዱ።
የልዑካን ቡድኑ ከአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ጋር በተወያዩበት ወቅት ፣ በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈንና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በሚከናወኑ ተግባራት ውስጥ የሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅን ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው ስልቶች ላይ በሰፊው መክረዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት የክልሉ ፖሊስ ተቋማዊ ሪፎርም ዋና አካል የሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅን በግንባር ቀደምትነት ማክበርና ማስከበር ነው ብለዋል።
“ወንጀልን የመከላከልና የህግ የበላይነትን የማስከበር ተልዕኮውን በሚወጣበት እያንዳንዱ እርምጃ የዜጎችን ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ማክበር ዋነኛ መርሆው ነው!” ሲሉ ኮሚሽነር ጀኔራሉ አጽንኦት ሰጥተው አብራርተዋል።
ኮሚሽነር ጀኔራሉ አክለውም ፖሊስ ከማህበረሰቡ ጋር በቅርበት በሚሰራቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ደህንነት ጥበቃ እና በምርመራ ሂደቶች ላይ አለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ አሰራሮችን ለመዘርጋት የICRC ድጋፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል።
የአለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ (ICRC) የቡድኑ ተወካይ ሳብሪና ዱናንክ እንደገለፁት በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችና በህግ አስከባሪ አካላት የስነ-ምግባር እሴቶች ዙሪያ ለፖሊስ አባላትና አመራሮች የሚሰጠውን ስልጠና አጠናክሮ እንዲቀጥል እንፈልጋለን። ተቋማችን ለዚህ አጋርነት አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ነው የፖሊስ አባላትን አቅም በመገንባት ረገድ የጋራ ትብብሩ የሚኖረውን ሚና ሲያብራሩ።
የልዑካን ቡድኑ መሪ በሰጡት አስተያየት የእኛ ዋና ዓላማ የሰብዓዊ መብት መርሆዎች በጸጥታ አካላት የዕለት ተዕለት የሥራ እንቅስቃሴ ውስጥ ሙሉ በሙሉ እንዲሰርጹ መደገፍ ነው። የአማራ ክልል ፖሊስ አመራር ለሰብዓዊ መብት መከበር ያሳየው ቁርጠኝነትና ግልጽነት ለቀጣይ ስራችን ትልቅ መተማመኛ ነው ብለዋል።
የአለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ (ICRC) የልዑካን ቡድን አባላት በበኩላቸው የአማራ ክልል ፖሊስ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥም ጭምር የህግ የበላይነትን ለማስከበርና የዜጎችን ሰላም ለመጠበቅ የሚያደርገውን ጥረት አድንቀዋል።
የቡድኑ አባላት አያይዘውም በቀጣይ በተለይም በቁጥጥር ስር ባሉ ተጠርጣሪዎች አያያዝ፣ በForensic (ፎረንሲክ) ምርመራ እገዛ እና በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ የሚሰጡ ስልጠናዎችን ተደራሽነት ይበልጥ ለማስፋትና ግንኙነቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
በማጠቃለያውም ሁለቱ አካላት የተጀመሩ የጋራ ስራዎችን ይበልጥ በተቀናጀ መልኩ ለማስቀጠልና በየደረጃው ያሉ የፖሊስ መዋቅሮችን አቅም ለማሳደግ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል።




