“ምርጫው በስኬት መጠናቀቁ የፖሊስ ሰራዊታችንን ዝግጁነትና ከፍተኛ የሙያ ስነ-ምግባር ያሳየበት ነው” ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር)

“ምርጫው በስኬት መጠናቀቁ የፖሊስ ሰራዊታችንን ዝግጁነትና ከፍተኛ የሙያ ስነ-ምግባር ያሳየበት ነው” ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር)

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ በክልሉ ዴሞክራሲያዊና ስኬታማ በሆነ መንገድ መጠናቀቁን አስመልክቶ ከስትራቴጅክና ከፍተኛ አመራሮቹ ጋር የግምገማ ማጠቃለያ አከናወኗል ።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ለምርጫው መሳካት የጸጥታ ኃይሉ ካሳየው ቁርጠኝነት ባሻገር ህዝቡ ለሰላም የሰጠው ዋጋ ትልቅ መሆኑን ገልጸዋል።

ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የክልሉን ሰላምና ደህንነት ለማናጋት አድፍጠው ይጠባበቁ ለነበሩ የውስጥና የውጭ የጥፋት ኃይሎች ተገቢው ምላሽ የተሰጠበት ታሪካዊ ክስተት ነው ብለዋል።

“ምርጫው ያለምንም የጸጥታ መደፍረስ በሰላም መጠናቀቁ የፖሊስ ሰራዊታችንን ዝግጁነት፣ ህዝባዊነትና ከፍተኛ የሙያ ስነ-ምግባር ያሳየበት ነው” ያሉት ኮሚሽነር ጀኔራሉ ከፌደረ‍ል የፀጥታ አካላት ፣ፓርቲዎች፣ ከምርጫ አስፈጻሚዎችና ከህብረተሰቡ ጋር የተደረገው የተቀናጀ ቅድመ-ዝግጅት ለዚህ ውጤት መገኘት ቀዳሚውን ሚና መጫወቱን አስገንዝበዋል።

ኮሚሽነር ጀኔራሉ አክለውም ፖሊስ ምርጫው ከመጀመሩ አስቀድሞ የሰላም ስጋት ሊሆኑ የሚችሉ ነጥቦችን በሳይንሳዊ መንገድ በማጥናትና የወንጀል መከላከያ ስትራቴጂዎችን በመቅረጽ በቁርጠኝነት መስራቱን ገልጸው፣ መላው የፖሊስ ሰራዊትና አመራር ላሳዩት ተጋድሎ ምስጋና አቅርበዋል።

ረዳት ኮሚሽነር አያልነህ ተስፋዬ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል እና የአስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ባቀረቡት ሪፖርት ከምርጫው በፊትና በምርጫው ዕለት ሊፈጠሩ የሚችሉ ግጭቶችን ለማስቀረት የተዘረጉት የጥበቃና የቁጥጥር ስልቶች ውጤታማ ነበሩ ብለዋል።

በተለይም የድምፅ መስጫ ቁሳቁሶች ወደየምርጫ ጣቢያው በሰላም እንዲጓጓዙና ሂደቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ ከመከላከያ ፣ ከክልሉ ፀጥታ ሀይሎች የነበረዉ ቅንጅት በከፍተኛ ንቃትና ሙያዊ ስነምግባር ግዴታውን ተወጥቷል ብለዋል።

ለሰራዊቱ የሚያስፈልጉ የትሎጂስቲክስ፣ የትራንስፖርትና የደህንነት ቁሳቁሶች በወቅቱና በጥራት እንዲደርሱ መደረጉ ሰራዊቱ ሙሉ ትኩረቱን በጸጥታ ስራው ላይ ብቻ እንዲያደርግ አስችሎታል ሲሉ የነበረውን ዝግጁነት አብራርተዋል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት ስትራቴጂክ እና ከፍተኛ አመራሮች በምርጫው ወቅት ያጋጠሙ መልካም ተሞክሮዎችንና የታዩ ክፍተቶችን በዝርዝር አንስተው ተወያይተዋል።

አመራሮቹ በሰጡት አስተያየት ህብረተሰቡ የፀጥታ አካሉን እንደራሱ አካል በመመልከት መረጃዎችን በፍጥነት በመስጠትና የሰላም ባለቤት በመሆን ያሳየው ትብብር ለስራቸው መሳካት ትልቅ አቅም እንደሆናቸው ገልጸዋል።

በምርጫው ሂደት የተገኘውን ይሄንን ጠንካራ የህዝብና የፖሊስ ትስስር (Community Policing) በቀጣይም የወንጀል ስጋቶችን ቀድሞ ለመከላከል በፍትሃዊነትና በቁርጠኝነት እንደሚጠቀሙበት ቃል ገብተዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የኮሙኒኬሽን እና ሕዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ በክልሉ የተካሄደውን 7ኛውን ሀገራዊ ምርጫ የጸጥታና ደኅንነት ሥራዎችን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።

ኃላፊው በመግለጫቸው ምርጫው ስኬታማ በሆነ መንገድ ተጠናቆ ለተፈለገው ዓላማ እንዲበቃ የጸጥታው መዋቅር ሌሊትና ቀን በቁርጠኝነት መሥራቱን አስታውቀዋል።

ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ እንደገለጹት የምርጫው ሂደት መጀመሪያውኑ ስጋቶች አስቀድመው የተለዩበት፣ የዕቅድ አፈጻጸሙም በአግባቡ በየደረጃው እየተገመገመና እየተመራ የመጣ በመሆኑ ሂደቱ በታላቅ ስኬት ሊጠናቀቅ ችሏል።

ለዚህ ስኬት ትልቁን ድርሻ የወሰደው የጸጥታ ኃይሉ የጋራ ቅንጅት መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊው፣ ከቀበሌ እስከ ክልል ድረስ ባሉት የጸጥታ መዋቅሮች መካከል ጠንካራና አስተማማኝ ትስስር መፍጠር በመቻሉ፣ ማንኛውንም ስጋት አስቀድሞ መከላከልና ሰላምን ማስከበር ተችሏል ብለዋል።

ይህ የተቀናጀ የጋራ ዕዝ አሠራር እና የጸጥታ መዋቅሩ ዝግጁነት ለሰላማዊው የምርጫ ሂደት ዋነኛ ምሰሶ መሆኑን አብራርተዋል።

ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ወቅት በምርጫው ወቅት እውነታውን ለሕዝብ ተደራሽ ሲያደርጉ ለነበሩ የሚዲያ አካላት ልዩ ምስጋና አቅርበዋል።

የሚዲያ ተቋማት የምርጫውን ሰላማዊነት በተመለከተ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃዎችን ለሕዝብ በማድረስ፣ የሕዝብ ዓይንና ጆሮ በመሆን ለተጫወታችሁት ሚና እና ላደረጋችሁት የላቀ አበርክቶ የክልሉ ፖሊስ ከፍተኛ ምስጋና ያቀርባል ሲሉ አስታውቀዋል።

በመጨረሻም ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ምርጫው በሰላም መጠናቀቁ ለቀጣይ የክልሉ ልማትና መረጋጋት ትልቅ መነሳሳትን የፈጠረ መሆኑን ጠቅሰው፤ አመራሩና መላው ሰራዊት የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ ለማድረግና የህግ የበላይነትን ለማስከበር የተጀመረውን ኦፕሬሽን ስራ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት እና የክልሉ የፀጥታ ሀይልም በራስ አቅም ህግ የማስከበር ስራዉን በተገቢ መንገድ እንዲወጣ አቅጣጫ በማስቀመጥ ስብሰባውን አጠናቀዋል።

ምርጫው በስኬት እንዲፈፀም ላደረጉት ዘርፎችም እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top