ለአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ አመራሮችና መምህራን በአለም አቀፍ ቀይ መስቀል የሰብአዊ መብት ስልጠና ተሰጡ።
በአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ለሚገኙ መምህራንና ከፍተኛ አመራሮች በአለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ (ICRC) አማካኝነት ለተከታታይ ሶስት ቀናት ሲሰጥ የነበረው ‘በሰብአዊ መብት አከባበር እና በፖሊስ ስራ’ ላይ ያተኮረ የአቅም ግንባታ ስልጠና በስኬት ተጠናቋል።
የዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ፕሬዘዳንት ምክትል ኮሚሽነር አበበ ደለለ በስልጠናው መዝጊያ ላይ እንደገለጹት ፖሊስነት አይተኬ ሚና ያለው አለም አቀፋዊ የህዝብ አገልግሎት በመሆኑ ሰብዓዊ መብትና የፖሊስ ስራ ምንጊዜም የማይነጣጠሉ ናቸው ብለዋል።
“ሰብአዊ መብቶችን የሚያከብር የፖሊስ ኃይል በሚያገለግለው ማህበረሰብ ዘንድ ጥልቅ እምነትን ይገነባል” ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ ፖሊስ ሁሌም ራሱን በማብቃት የሰዎችን ሰብአዊ መብትና ደህንነት ማስከበር እንዳለበት አሳስበዋል።
ምክትል ኮሚሽነሩ አክለውም ለአለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ (ICRC) ምስጋናቸውን አቅርበው በቀጣይም በጋራ አውደ ጥናቶች፣ በስርዓተ ትምህርት ቀረጻ እና በሞጁል ዝግጅቶች ላይ አብሮ ለመስራት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ዝግጁና ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።
የአለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ የሰራዊትና ደህንነት ክፍሎች (Armed and Security Force) ተወካይ ሚስተር ኦቪዱ ቫሰሊካ በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ተገኝተው ስልጠና በመስጠታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ይህ ስልጠና ተቋሙ ለሚያሰለጥናቸው እጩ ፖሊሶች የሰብዓዊ መብት አከባበርን ከፖሊስ ስራ ጋር አቆራኝቶ በቂ እውቀት ለመስጠት እንደሚያስችለው ጠቁመው በቀጣይም አጋርነታቸው እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል።
ተወካዩ አክለውም ICRC በኢትዮጵያ በየትኛውም አካባቢ ከማንኛውም ፖለቲካዊ ወገንተኝነት ነፃ በመሆን የሰብዓዊ መብት አያያዝ ትምህርትና ስልጠና አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።
በመጨረሻም የሰልጠናው ተሳታፊዎች ስልጠናው ለቀጣይ ስራቸው ትልቅ አቅም የሚሆን በቂ ዕውቀት ያገኙበት መሆኑን በመግለጽ መሰል አጫጭር የስራ ላይ ስልጠናዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
የኮሌጁ ፕሬዝዳንትም ሰልጣኞች ያገኙትን እውቀትና ክህሎት ወደ ተግባር በመቀየር በሚሰጧቸው ስልጠናዎች ላይ እንዲተገብሩት አደራ በማለት ስልጠናው ተጠናቋል።







