የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ስትራቴጂክ አመራሮች ከፖሊስ አመራር እና አባላት ጋር ተቋም አቅም ግንባታና የሪፎርም ስራዎች ጋር በተያያዘ ውይይት አካሄዱ።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ስትራቴጂክ አመራሮች ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን እና ከጎንደር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ አመራርና አባላት ጋር ወቅታዊ የፀጥታ ተልዕኮዎችንና ተቋማዊ ሪፎርሞችን በተመለከተ በጎንደር ከተማ የምክክር መድረክ አካሄዱ።
በመድረኩ ላይ የሰራዊቱ ወቅታዊ የግዳጅ አፈፃፀም፣ የስምሪት ሁኔታ እና የፀጥታ ስራዎች የተገመገሙ ሲሆን ለቀጣይ ስራዎችም አቅጣጫ ተቀምጧል።
የምክትል ኮሚሽነር ጀኔራልና የአስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ረዳት ኮሚሽነር አያልነህ ተስፋዬ፣ የኮሚሽነር ጀኔራል ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር የሽወርቅ ላቀው እና የአድማ መከላከል ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር አወቀ ሞትባይኖር መድረኩን መርተዋል።
አመራሮቹ በንግግራቸው የፖሊስ ሰራዊቱ የሕዝብን ሰላምና የሕግ የበላይነት ለማረጋገጥ የከፈለው መስዋዕትነትና ያስመዘገበው ድል ታሪክ የማይረሳው መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህም የክልሉ መንግስት እና ዋና ጠቅላይ መምሪያው ተገቢውን እውቅና እየሰጡት መሆኑን አስታውቀዋል።
ረዳት ኮሚሽነር አያልነህ ተስፋየ የፖሊስን ሙያዊ ብቃት፣ ተጠያቂነትና የአገልግሎት ጥራት ለማሻሻል እየተተገበረ ያለው ተቋማዊ ሪፎርም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
እያንዳንዱ የሰራዊት አባል የለውጥ ስራውን እንደራሱ ጉዳይ በመቁጠር በትጋት ሊሰራ እንደሚገባም አክለዋል።
ረዳት ኮሚሽነር የሽወርቅ ላቀው የኮሚሽነር ጀኔራል ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በበኩላቸው የክልሉ ፖሊስ ከፌደራል የፀጥታ ኃይሎች ጋር በቅንጅት በመስራት የጠላትን ሥነ-ልቦና መስበር የቻለ ጠንካራ ቁመና ላይ ደርሷል ብለዋል።
በቀጣይም ይህ የጋራ ስራና የህዝብ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ፖሊሳዊ ተልዕኮዎችን ሙያዊ ዲስፕሊን በጠበቀ መንገድ ልትወጡ ይገባል ሲሉ ረዳት ኮሚሽነር የሽወርቅ ላቀው አሳስበዋል።
ረዳት ኮሚሽነር አወቀ ሞትባይኖር የአድማ መከላከል ዋና መምሪያ ኃላፊ የፖሊስ አባላት የከፈሉት መስዋዕትነት እና ያሳዩት ቁርጠኝነት የሚያኮራ መሆኑን አስረድተዋል።
የክልሉ ሰላም ሊረጋገጥ የቻለው በተቀናጀ የፀጥታ ሥራ፣ በሕዝብ ድጋፍ እና በሰራዊቱ የማይናወጥ ቁርጠኝነት መሆኑን የጠቀሱት ረዳት ኮሚሽነር አወቀ በቀጣይም ሕዝብን በማገልገልና ሕግን በማስከበር ረገድ የተጀመሩ ጠንካራ ሥራዎች በበለጠ ትጋት እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
የውይይት መድረኩ ከአባላቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ሰፊ ማብራሪያ በመስጠት የተጠናቀቀ ሲሆን የሰራዊቱን አንድነት፣ የሥራ መነሳሳትና የተልዕኮ አፈፃፀም ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተገልጿል።







