በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የፖሊስ ሰራዊት የግዳጅ አፈጻጸም እና የመስክ ምልከታ ተካሄደ።
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በጎርጎራ፣ በመገጭ፣ በእንፍራንዝ እና በምዕራብ ደንቢያ አካባቢ የተሰማራውን የፖሊስ ሰራዊት የግዳጅ አፈጻጸም ለመገምገም እና ያለበትን ተጨባጭ ሁኔታ ለመመልከት የሚያስችል የመስክ ምልከታ ተካሂዷል።
በዚህ የመስክ ምልከታ ላይ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ስትራቴጂክ አመራሮች ተገኝተው ከሰራዊቱ ጋር ውይይት አድርገዋል።
የመስክ ምልከታውን አስመልክቶ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የአስተዳደር እና ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ረዳት ኮሚሽነር አያልነህ ተስፋዬ ሰራዊቱ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ እየከፈለ ያለው መስዋዕትነት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።
አዛዡ አክለውም ሰራዊቱ የተሰጠውን ግዳጅ በላቀ የባለሙያ ብቃትና በጽናት መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።
የአስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያው የሰራዊቱን የግዳጅ አፈጻጸም ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችሉ የሎጂስቲክስና የልማት ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል።
የዋና ጠቅላይ መምሪያው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር የሽወርቅ ላቀ በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር የወቅቱን የጸጥታ ሁኔታ ያገናዘበ ግልጽና የተቀናጀ የኮሙኒኬሽንና የዕዝ ሰንሰለት መኖር ለግዳጅ ስኬታማነት ያለውን ሚና አብራርተዋል።
ሰራዊቱ ከተሰማራበት ማኅበረሰብ ጋር የጠበቀ ትስስር በመፍጠር የሕዝብን አመኔታ ባተረፈ መልኩ የሕግ የበላይነትን የማስከበር ተልዕኮውን በኃላፊነት ስሜት ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል።
የወንጀል መከላከል ስራዎችን ስትራቴጂያዊ አቅጣጫ በተመለከተ የአድማ መከላከል ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር አወቀ ሞትባይኖር በሰጡት አስተያየት በዞኑ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ስጋት ሊሆኑ የሚችሉ የወንጀልና የጸጥታ ችግሮችን አስቀድሞ በመከላከል ረገድ ሰራዊቱ እያከናወነ ያለው ስራ ውጤታማ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይሁን እንጂ የሕዝብን ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ የጸጥታ ስጋቶችን በሳይንሳዊና በተደራጀ መንገድ የመተንተንና የመከላከል አቅምን ማሳደግ ቀጣይ የቤት ስራ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በምልከታው ወቅት የሰራዊቱ አባላት በሰጡት ሀሳብ የተጣለባቸውን የህዝብ ወገንተኝነትና ሙያዊ ኃላፊነት ጠንቅቀው እንደሚረዱ ገልጸዋል።
ከከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች የተሰጡትን አቅጣጫዎች መነሻ በማድረግ የክልሉን ሰላምና የሕዝቡን ደኅንነት ለማረጋገጥ የተሰጣቸውን ማንኛውንም የግዳጅ ተልዕኮ እስከ መስዋዕትነት ድረስ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን በቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
ይህ የመስክ ምልከታ በዞኑ የሚገኘውን የሰራዊት አባል የስነ-ልቦና ዝግጁነት ከማሳደጉም በላይ በቀጣይ ለሚከናወኑ የጸጥታና የሕግ ማስከበር ስራዎች ትልቅ አቅም የፈጠረ መሆኑ ተገልጿል።








