የጸጥታ ኃይሉን የግዳጅ አፈጻጸምና የሰላም ስራዎችን በላቀ ዝግጁነት ለመምራት የሚያስችል የግንባር ምልከታና ውይይት ተካሄደ።

የጸጥታ ኃይሉን የግዳጅ አፈጻጸምና የሰላም ስራዎችን በላቀ ዝግጁነት ለመምራት የሚያስችል የግንባር ምልከታና ውይይት ተካሄደ።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ስትራቴጂክ አመራሮች በደቡብ ወሎ ዞን አልብኮ ወረዳ በመገኘት በግንባር ምልከታና በውይይት የታጀበ የፖሊስ ሰራዊት ማበረታቻ መርሃ-ግብር አካሄዱ።

በዚሁ የመስክ ምልከታና የውይይት መርሃ-ግብር ላይ የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ስትራቴጅክ አመራሮች፣ የዞንና የወረዳው የጸጥታ መዋቅር ኃላፊዎች እንዲሁም የፖሊስ ሰራዊት አባላት ተገኝተዋል።

በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር አበበ ውቤ እንደገለጹት በአልብኮ ወረዳ የተሰሩ ሁሉን አቀፍ የወንጀል መከላከል እና ህግ የማስከበር ስራዎች አበረታች ናቸው። ለዚህ ውጤታማ ስራ መገኘት የአካባቢው ማህበረሰብና የወረዳው አስተዳደር ከሰራዊቱ ጎን መቆማቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት የሰራዊቱ ዝግጁነት በላቀ ደረጃ ላይ እንደሚገኝና በቀጣይም ዘላቂ ሰላምን የሚያረጋግጡ ተግባራት ላይ ትኩረት እንደሚደረግም ምክትል ኮሚሽነር አበበ ውቤ አስታውቀዋል።

የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው በበኩላቸው 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ያለምንም የፀጥታ ስጋትና ሁከት በስኬት እንዲጠናቀቅ መደረጉን አስታውሰዋል።

ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በጥምረትና በትኩረት በመስራቱ ምርጫው በሰላም መጠናቀቁን የገለጹት ምክትል ኮሚሽነሩ ከምርጫው በፊት የተሰጡ የሥነ-ምግባር እና የአፈፃፀም ስልጠናዎች ሙያዊና ተቋማዊ ኃላፊነትን በብቃት ለመወጣት ትልቅ አቅም መፍጠራቸውን አብራርተዋል።

የፀጥታ መዋቅሩ ለክልሉ ሰላም መጠበቅ ትልቅ ዋጋ በመክፈሉ በአሁኑ ወቅት የተሻለ ሰላም እንዲሰፍን አድርጓል ያሉት ደግሞ ረዳት ኮሚሽነር አብዮት ሽፈራው የሰው ሀብት አስተዳደርና ልማት ዋና መምሪያ ኃላፊ ናቸው።

የደቡብ ወሎ ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር አሳምነው ሙላት ህብረተሰቡ የተረጋጋ ህይወት እንዲመራ በተሰሩ የጸጥታ ማስፈንና ወንጀል መከላከል ስራዎች ላይ ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።

በቀጣይም የተገኘውን ሰላም የማጽናት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ኮማንደር አሳምነው ሙላት የደቡብ ወሎ ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ አረጋግጠዋል።

በመጨረሻም የፖሊስ ሰራዊት አባላት ህብረተሰቡ የልማት ተጠቃሚ እንዲሆንና ሰላሙ በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲቀጥል ጀግንነት የተሞላበት ዋጋ እየከፈሉ መሆናቸውን በመግለጽ፣ በቀጣይም የተጀመረውን ዘላቂ ሰላም የማረጋገጥ ተልዕኮ በላቀ ቁርጠኝነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን በፅናት አረጋግጠዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top