“በምርምርና ፈጠራ የታገዘ ፖሊሳዊ አገልግሎት ለዘላቂ ሰላም፤” 4ኛው የምርምር ሲምፖዚየም በአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተካሂዷል።

“በምርምርና ፈጠራ የታገዘ ፖሊሳዊ አገልግሎት ለዘላቂ ሰላም፤” 4ኛው የምርምር ሲምፖዚየም በአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተካሂዷል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ “ምርምርና ፈጠራ ለተሻለ የፖሊስ አገልግሎት እና ዘላቂ ሠላም!” በሚል መሪ ቃል ሲካሄድ የቆየው 4ኛው የምርምር ሲምፖዚየም ተጠናቋል።

በዚህ መድረክ ላይ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች፣ የፖሊስ ስትራቴጂክ እና ከፍተኛ አመራሮች፣ ተመራማሪዎችና የዘርፉ ምሁራን ታድመዋል።

በሲምፖዚየሙ መክፈቻ ላይ መሪ ቃሉን መነሻ በማድረግ ቁልፍ ንግግር ያደረጉት ረዳት ኮሚሽነር ግዛቸው ከበደ የዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ የአካዳሚክስ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት እንደገለጹት ወቅቱ የሚጠይቀውን ቀልጣፋ፣ ዘመናዊና ውጤታማ የፖሊስ አገልግሎት ለመስጠት የምርምርና የፈጠራ ስራዎች ወሳኝ ሚና አላቸው።

ይሄንን ሳይንሳዊ መንገድ መከተል ለአካባቢው ህዝብ አስተማማኝና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ጠንካራ መሰረት ይጥላል ሲሉ ረዳት ኮሚሽነር ግዛቸው ከበደ አክለው አብራርተዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የ6ኛ ዕዝ አዛዥ ሜጀር ጀኔራል ብርሃኑ ጥላሁን በበኩላቸው፤ በምርምር የተደገፈ ፖሊሳዊ አገልግሎት መስጠት በክልሉ አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን ለሚደረገው ጥረት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

ከጸጥታ መዋቅሩ ጎን ለጎን የጥናትና ምርምር ተቋማት የሚያመነጯቸው ግኝቶች በወረቀት ላይ ብቻ መቅረት እንደሌለባቸውና በተግባር ላይ መዋል እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዝዳንት ምክትል ኮሚሽነር አበበ ደለለ በበኩላቸው የወቅቱ የጸጥታና ደህንነት ሁኔታ ፖሊሳዊ አገልግሎቱ ካለበት ልማዳዊ አሰራር ወጥቶ ወደ ላቀ ሳይንሳዊ ምዕራፍ እንዲሸጋገር እንደሚያስገድደው በስፋት አብራርተዋል።

የክልሉ የፖሊስ ሰራዊት በንድፈ-ሀሳብ ብቻ ሳይሆን በዘመናዊ እውቀት፣ በተግባራዊ ክህሎት እና በከፍተኛ ስነ-ምግባር የታነጸ ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል።

“የእኛ ዋና ተልዕኮ ህዝብን በታማኝነት፣ በቅንነትና በሙያዊ ብቃት ማገልገል ነው። ይህንን ለማሳካት ደግሞ ሰራዊታችን በየደረጃው የህዝብን ደህንነት በዘላቂነት ማረጋገጥ የሚያስችል የዕውቀትና የክህሎት ባለቤት መሆን አለበት” ሲሉ ምክትል ኮሚሽነር አበበ ደለለ አጽንኦት ሰጥተው አብራርተዋል።

ፕሬዝዳንቱ አያይዘውም ይህ 4ኛው የምርምር ሲምፖዚየም እንዲሁ በየዓመቱ የሚደረግ ተራ ስብሰባ ሳይሆን፣ የአማራን ህዝብ ሰላምና ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለማስጠበቅ የሚያግዙ ስልታዊ አቅጣጫዎች የሚቀመጡበት መድረክ መሆኑን ጠቁመዋል።

መድረኩ በተጨባጭ መሬት ላይ ያሉ የጸጥታ ፈተናዎችን በሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር በተደገፈ አሰራር ለመፍታት እና አዳዲስ ስልቶችን ለመንደፍ የሚያስችል ዋና የዕውቀት መፍለቂያ መሆኑንም ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ በአሁኑ ወቅት የነገውን ፖሊስ የመገንባት ትልቅ ራዕይ ሰንቆ እየሰራ መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ኮሚሽነሩ በተለይም በቴክኖሎጂ አጠቃቀም የበቃ፣ ከዘመኑ ጋር እኩል የተራመደ እና በቴክኒክና ታክቲክ የላቀ ዘመናዊ የፖሊስ ሰራዊት ለመገንባት በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

የወንጀል መከላከልም ሆነ የምርመራ ስራዎች በቴክኖሎጂ ሲታገዙ የህዝቡን እምነት የሚያተርፍና አጥፊዎችን በቀላሉ ለህግ የሚያቀርብ ተቋም መፍጠር እንደሚቻልም በዝርዝር አስገንዝበዋል።

በሲምፖዚየሙ ላይ ጥናታዊ ጽሑፎች የቀረቡ ሲሆን፤ ከነዚህም መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦

• “Police operational roles and crime prevention effectiveness in volatile security context”

• “Challenges of policing in enforcing law and public order during armed conflict”

• “Unpacking predictors of police violence in Ethiopia: A post-1991 perspective”

• “Examining the effect of authentic and transformational leadership styles on police officers’ motivation”

• “Police education and training as drivers of police reform in Ethiopia”

በቀረቡ ጥናታዊ ጽሑፎች ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top