“በህዝብና በፖሊስ መካከል ያለው መተማመን የሰላም ዋስትናችን ነው!!” አቶ ተሾመ ዋለ

“በህዝብና በፖሊስ መካከል ያለው መተማመን የሰላም ዋስትናችን ነው!!” አቶ ተሾመ ዋለ

የደብረማርቆስ ከተማ አስተዳደር ከጸጥታ መዋቅሩና ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት በመስራት የከተማዋን አስተማማኝ ሰላምና ደህንነት የማስቀጠል፣ ህገ-ወጥነትን የመግታት እንዲሁም የጸጥታ መዋቅሩን የማዘመን ስራዎችን በስፋት እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ።

የደብረማርቆስ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ተሾመ ዋለ ከአማራ ፖሊስ ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ የህግ የበላይነትን በማረጋገጥና የህዝብ ተሳትፎን በማጎልበት የከተማዋን አስተማማኝ ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ሌሊትና ቀን እየተሰራ ነው።

እንደ አቶ ተሾመ ዋለ ገለጻ በአሁኑ ወቅት በከተማዋ ያለው አጠቃላይ የጸጥታ ሁኔታ አስተማማኝና የተረጋጋ በመሆኑ፣ ነዋሪው ያለ ምንም ስጋት የእለት ተእለት የንግድ፣ የማህበራዊና የልማት እንቅስቃሴዎቹን በሙሉ አቅሙ እያከናወነ ይገኛል።

የጸጥታ መዋቅሩን በተቀናጀ መልኩ ወደ ስራ ማስገባትና የህግ ማስከበር ስራዎችን በልዩ ትኩረት ማከናወን መቻሉን የገለጹት አቶ ተሾመ፤ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ያካሄደው ሪፎርምና በየደረጃው የሰጠው ስልጠና የፖሊስ ሰራዊቱ በስነ-ምግባር የታነጸና የህዝብ አለኝታነቱን በተግባር የሚያሳይ እንዲሆን ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አብራርተዋል።

“በህዝብና በፖሊስ መካከል ያለው መተማመን የሰላም ዋስትናችን ነው!!” ሲሉ ያብራሩት አቶ ተሾመ ዋለ ፖሊስ ለህዝብ ጥቆማ ፈጣንና ሚስጥራዊነቱ የተጠበቀ ምላሽ እንዲሰጥ በማድረግ የጋራ መተማመኑን ይበልጥ እያሳደግን እንገኛለን ብለዋል።

የከተማዋ ሰላም መሰረቱ ህዝቡ መሆኑን የጠቀሱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው፤ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሴቶችና ከወጣቶች ጋር የተደረጉ ተከታታይ ውይይቶች እጅግ ውጤታማ እንደነበሩ ገልጸው፤ የጸጥታ ስጋቶችን አስቀድሞ ለመከላከል የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት (ኮሚኒቲ ፖሊሲንግ) ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል።

የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ቢምረው አሰፋ በበኩላቸው፤ ቀደም ሲል በከተማዋ ይፈጸሙ የነበሩ ከባድ ወንጀሎችን በመከላከልና ወንጀል ፈጻሚዎችን በሕግ ጥላ ሥር በማዋል ረገድ ሰፊ ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል።

ይህ የተሳካ የጋራ ኦፕሬሽን ሊገኝ የቻለው ከሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከአጋር የዞኑ የጸጥታ አካላት፣ ከአጎራባች ዞኖችና ወረዳዎች ጋር በተደረገ የተቀናጀ አሰራር መሆኑንም ጠቁመዋል።

የህግ ማስከበር ስራችንን ይበልጥ ተቋማዊና የተደራጀ በማድረግ ለነዋሪዎች፣ ለባለሀብቶችና ለነጋዴዎች ምቹና አስተማማኝ ከባቢ እንፈጥራለን ሲሉ የፖሊስ መምሪያ አዛዡ አክለዋል።

ወጣቶች የጥፋት ኃይሎች መጠቀሚያ እንዳይሆኑና የከተማቸውን ሰላም በንቃት እንዲጠብቁ ለማስቻል ሰፊ ስራዎች በቅንጅት እየተሰሩ እንደሆነ አብራርተዋል።

በከተማዋ አርዓያነት ያለው የሕግ ማስከበር ሥራ እየሰሩ ከሚገኙ የፖሊስ ጣቢያዎች መካከል የ2ኛ እና የ4ኛ ፖሊስ ጣቢያ አዛዦች ኢንስፔክተር ብሩክ ሁናቸው እና ኢንስፔክተር አወቀ አያሌው እንደገለጹት፤ ማህበረሰቡን በጥበቃ ስራ በማደራጀት እና ከሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን የተጠናከረ የሌሊት የቅኝት (ፓትሮል) እና የኬላ ፍተሻ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።

ቀደም ሲል በህገ-ወጥ ታጣቂ ቡድኖች ሊሰነዘሩ የነበሩ ጥቃቶችን በጀግንነት ማክሸፍና ወንጀሎችን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ መቻሉንም አክለው አብራርተዋል።

የከተማዋ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት፤ ቀደም ሲል ይስተዋሉ የነበሩ ስጋቶች ተወግደው አሁን ላይ ሙሉ እፎይታ መፈጠሩን ገልጸዋል።

ነዋሪዎቹ አክለውም፣ ፖሊስ ከህብረተሰቡ ጋር በቅርበት እየሰራ ማህበረሰቡን በጥበቃ ስራ ላይ ማደራጀቱ ሌሊትም ሆነ ቀን በነጻነት ተንቀሳቅሰው እንዲሰሩ ትልቅ የደህንነት ዋስትና እንደሆናቸው በመግለጽ፣ የተገኘውን ሰላም ለማስቀጠል ከጸጥታ አካላት ጎን መቆማቸውን አረጋግጠዋል።

በመጨረሻም አቶ ተሾመ ዋለ ለጸጥታ ኃይሉ እስካሁን ላሳዩት ህዝባዊ ወገንተኝነትና የጀግንነት ተግባር ምስጋና አቅርበው፤ የተጀመረውን የተደራጀና ስነ-ምግባራዊ አሰራር ይበልጥ እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የከተማው ነዋሪዎችም የተገኘውን ሰላም እንደ አይን ብሌን እንዲጠብቁና በጸጥታ ስራዎች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያጠናክሩ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፤ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የሕገ-ወጥ ታጣቂ ቡድኑ አባላትም ይህንን አጋጣሚ ተጠቅመው የሰላምን አማራጭ እንዲቀበሉ ጥሪ አቅርበዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top