የኮሙኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነት ተግባር በሪፎርሙ በመንግስትና በህብረተሰቡ መካከል ጠንካራ መተማመንን በመፍጠር ፤ ተቋማዊ ስኬቶችንና መልካም ገፅታን ለህዝብ በማንፀባረቅ ረገድ ግንባር ቀደም መሳርያ መሆኑ ተገለጸ።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር)ን ጨምሮ ከፍተኛና ስትራቴጅክ አመራሮች በሚዲያና የህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ የተከናወኑ የሪፎርም ስራዎችን ጎበኙ።
በጉብኝቱም ለሚዲያና ህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ምቹ የስራ ሁኔታን ለመፍጠር የተከናወኑ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችና የቢሮ ማሻሻያ ስራዎች ተገምግመዋል።
የክልሉ ፖሊስ ዋና አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የኮሚኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ የተቋሙን አጠቃላይ ገፅታ በመገንባት፣ የፖሊስን መልካም ስራዎች ለህዝብ በማሳየት እንዲሁም በፖሊስና በህብረተሰቡ መካከል ጠንካራ መተማመንን በመፍጠር ረገድ የተጣለበትን ኃላፊነት በሚገባ እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ሪፎርሙ ትኩረት ከሰጠባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል የሚዲያና ህዝብ ግንኙነት ዘርፉን ማዘመን አንዱ መሆኑን የጠቀሱት ኮሚሽነር ጀነራሉ፤ በእውቀት የዳበረ፣ ከዘመናዊ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ጋር የተላመደ የሰው ኃይል በመገንባትና ምቹ የስራ ሁኔታን በመፍጠር ረገድ ተስፋ ሰጪ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ሚዲያ የፀጥታ አካሉንና ህዝቡን በማቀራረብ፣ የወንጀል መከላከል ስራዎችን ውጤታማ በማድረግ፣የፖሊስ ሰራዊቱን የግዳጅ አፈፃፀም በማሳየት ፣የአግልግሎት አሰጣጥና የወደፊት ተቋማዊ ዕቅዶችን ለህዝብ በማስተዋወቅ እና የተቋሙን አወንታዊ ገፅታ በመገንባት ረገድ ሚዲያ ክፍሉ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን አፅንኦት ሰጥተዋል።
እንደ ኮሚሽነር ጀነራሉ ገለፃ፤ የፖሊስ ስፖርት ክፍል ከአገር ውስጥ አልፎ በዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ጭምር ውድድሮችን በመሳተፍ፣ አመርቂ ድሎችን በማስመዝገብና የተቋሙን ስም በበጎ በማስጠራት ረገድ ታላቅ አምባሳደራዊ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ከአገር ውስጥ እስከ ውጭ ሀገር የተቋሙን ገፅታ በከፍተኛ ደረጃ እየገነባ የሚገኘው የስፖርት ክፍል፤ ይበልጥ ውጤታማና የላቀ የድል ባለቤት ለማድረግም ቀጣይነት ያለውና የተጠናከረ የቅርብ ክትትል፣ ሙያዊ አመራርና ሁለንተናዊ ድጋፍ ሊደረግለት እንደሚገባ ተመላክቷል።
የተቋሙን ገፅታ በመገንባትና ከህዝብ ጋር ያለውን ትስስር በማጠናከር ረገድ ከሚዲያውና ከስፖርቱ ባሻገር የኪነ-ጥበብ (የቲያትርና ሙዚቃ) እና የማርች ባንድ ቡድኖች ያላቸው ሚና የላቀ መሆኑንም አንስተዋል።
የቴያትርና ሙዚቃ እና የማርች ባንድ ክፍሎች ፖሊስንና ህዝብን በባህልና በስነ-ጥበብ መድረኮች በማገናኘት፣ የኮሚሽኑን ሰብአዊ፣ ህዝባዊና ሰላማዊ ወገንተኝነት በህብረተሰቡ ልብ ውስጥ እንዲሰረጽ በማድረግ ረገድ ትልቅ አቅም በመሆናቸው፤ በተቀናጀና በተደራጀ መልኩ በትኩረት እንደሚሰራበት አረጋግጠዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነርና የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው በበኩላቸው በኮሙኒኬሽን እና ህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ በኩል የተሰሩ የሪፎርም ስራዎች አስደሳችና ለሰራተኞች የስራ መነሳሳትን የሚፈጥሩ ናቸው ብለዋል።
ዋና መምሪያው ተቋሙን ከህዝብ ጋር በማገናኘት እንደ ድልድይ ሆኖ በማገልገል የሰራቸው ስራዎችም ውጤት ማምጣታቸውንም ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው አክለው ገልፀዋል።
ረዳት ኮሚሽነር የሽወርቅ ላቀው በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የኮሚሽነር ጀነራል ፅህፈት ቤት ኃላፊ እንደሚሉት የክልሉ ፖሊስ ተቋም ትኩረት ከሚሰጣቸው የሙያ ዘርፎች ውስጥ የኮሙኒኬሽን እና ህዝብ ግንኙነት ሙያ አንዱ በመሆኑ ከተሰራው ምቹ የስራ አካባቢን የመፍጠር ስራ ባለፈ ሙያን የሚያሳድጉና ክህሎትን የሚያጎለብቱ ስራዎች ላይ ያተኮረ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ዋና መምሪያው በሰው ሀይል ግንባታ፣በምቹ አካባቢ ፈጠራና ሙያን ለማሳደግ ባደረገው ጥረት ውጤት መገኘቱን የጠቀሱት ኀላፊው ይህን መልካም ተግባር አጠናክሮ በማስቀጠል ተቋሙን የሚያሳድጉና ተወዳዳሪ የሚያደርጉ ስራዎችን መስራት እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል።
በተቋሙ የኮሙኒኬሽን እና ህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ በበኩላቸው የኮሙኒኬሽን እና ህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪየአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ያደረገውን የሪፎርም ስራ እና የተቋሙን ተግባር እና ሀላፊነት ካስመዘገባቸው አመርቂ ውጤቶች ጋር በማጣመር ለማህበረሰቡ ተደራሽ በማድረግ በፖሊስ እና ማህበረሰቡ መካከል መልካም ግንኙነት እንዲፈጠር ያስቻለ ነው ብለዋል።
ሙያውን ለማዳበርና የሰራተኛውን የመስራት ተነሳሽነት ለማጎልበት የተሰሩ የሪፎርም እና የልማት ስራዎች ከተቋሙ የለውጥ ስራዎች ውስጥ በመሆናቸው በቀጣይም በሁሉም የሙያ ዘርፍ ውጤታማ ስራን ለማስመዝገብ በትኩረት እየተሰራ ነው።
ኮማንደር መሳፍንት እሸቴ በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የጥገና መምሪያ ኃላፊ እንደተናገሩት የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ከሰራቸው የሪፎርም ስራዎች መካከል ምቹ የስራ አካባቢን በመፍጠር የሰራተኛውን የመስራት ሞራል ማሳደግ በመሆኑ የኮሙኒኬሽን እና ህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ የሰራቸው ስራዎች ለዚህ የለውጥ ስራ አንዱ ማረጋገጫ ነው ብለዋል።
በቀጣዩ በጀት ዓመት በሁሉም ዘርፍ የሙያ ስልጠና ለመስጠት ዕቅድ መያዙንና የተጓደሉ የመስሪያ ቁሳቁሶችን ደረጃ በደረጃ በማሟላት ፈጣንና ጥራት ያለው አገልግሎት ለህዝብ ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ ተመላክቷል። ይህ የቁሳቁስ ማሟላት ሂደትም በየትኛውም ቦታ ተወዳዳሪና ተፈላጊ የሆነ ባለሙያ ለመፍጠር ታስቦ እየተሰራበት ያለ ተግባር መሆኑ ተጠቁሟል።












