የዘንድሮው የአረፋ በዓል ያለምንም የጸጥታ ስጋት በሰላም እንዲጠናቀቅ አስተማማኝ የሰው ኃይል ስምሪትና ሰፊ የደህንነት ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለጸ።

የዘንድሮው የአረፋ በዓል ያለምንም የጸጥታ ስጋት በሰላም እንዲጠናቀቅ አስተማማኝ የሰው ኃይል ስምሪትና ሰፊ የደህንነት ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለጸ።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች ለ1447ኛው የዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል እንኳን አደረሳችሁ እያለ መልካም ምኞቱን ይገልጻል።

የአረፋ በዓል የእስልምና እምነት ተከታዮች እርስ በርስ የሚተሳሰቡበት፣ የተቸገሩትን ወገኖች የሚረዱበትና ማህበረሰቡ በአንድነት ፍቅርን፣ ሰላምንና መከባበርን የሚያሳይበት ታላቅ ሃይማኖታዊና ማህበራዊ እሴት ነው።

ይህ መልካም እሴት ተጠብቆ በዓሉ በሰላምና በደስታ እንዲጠናቀቅ የክልላችን የጸጥታ ኃይል ሌት ተቀን በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል።

የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ማስጠበቅ ዋነኛ ተግባሩ ያደረገው የጸጥታ መዋቅራችን፣ በዓሉ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲከበር ልዩ ትኩረት በመስጠት ሰፊ ዝግጅት አድርጓል።

በዓሉ በሚከበርባቸው የመስገጃ ቦታዎችና ክፍት አደባባዮች ላይ በቂ የሰው ኃይልና የሎጂስቲክስ ስምሪት ዝግጅቱ ተጠናቋል።

የሙስሊሙ ማህበረሰብ ያለምንም የስጋት መንፈስ በዓሉን እንዲያከብር ከሌሎች የጸጥታ አካላትና ከበዓሉ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ጋር የጠበቀ የጋራ ቅንጅት ተፈጥሯል።

ሰላም በጋራ ጥረትና በትብብር የሚረጋገጥ የጋራ እሴት በመሆኑ፣ በዓሉ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ይዘቱን ሳይለቅ፣ ፍጹም ሰላማዊና ድምቀት ያለው ሆኖ እንዲያልፍ ህብረተሰቡ የበኩሉን ከፍተኛ ድጋፍ እንዲያደርግ ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል።

በዚህም መሰረት ህብረተሰቡ ንቁ የሰላም ባለቤት በመሆን በአካባቢው አጠራጣሪ ነገሮችን፣ ጸጉረ-ልውጥ አዲስ ሰዎችን ወይም የሰላም መደፍረስ ምልክቶችን ሲመለከት በአቅራቢያው ለሚገኙ የጸጥታ አካላት በአስቸኳይ በመጠቆም ዜጋዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ተጠይቋል።

የበዓሉን መንፈስ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ፣ እርስ በርስ በመረዳዳት፣ አቅም የሌላቸውን፣ የተፈናቀሉና የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ እንዲሁም በማዕድ ማጋራት ማሳለፍ እንደሚገባ ተገልጿል።

የህግ የበላይነትን ከማክበር አኳያም በበዓሉ ስነ-ስርዓት ላይ ትርምስ የሚፈጥሩ፣ ጸብ የሚጭሩ ወይም የህዝብን ሰላም የሚያናጉ አጋጣሚዎችን ከመፍጠር መቆጠብና መሰል ድርጊቶች ሲያጋጥሙ ለህግ አስከባሪዎች ጥቆማ መስጠት እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል።

ማህበረሰቡ እንደተለመደው ከጸጥታ ኃይሉ ጎን በጽናት በመቆም አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ የሰላሙ ዋና ባለቤት እንዲሆን የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ጥሪውን አስተላልፏል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በድጋሚ ለመላው የእምነቱ ተከታዮች በዓሉ የፍቅር፣ የደስታ፣ የበረከትና የሰላም እንዲሆን ይመኛል።

መልካም የዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል!

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top