“የመንገድ ትራፊክ ደኅንነትን ለማስጠበቅ ስኬታማ ተግባራት እየተከናወነ ነው!”

“የመንገድ ትራፊክ ደኅንነትን ለማስጠበቅ ስኬታማ ተግባራት እየተከናወነ ነው!”

የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ 4ኛ ፖሊስ ጣቢያ የመንገድ ትራፊክ ደኅንነትን በማስጠበቅ ረገድ አመርቂ ስኬት እያስመዘገበ መሆኑ ተገለፀ።

በደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ የ4ኛ ፖሊስ ጣቢያ የመንገድ ትራፊክ ደኅንነትን በማስጠበቅ፣ የትራፊክ አደጋን በመቀነስና የከተማዋን የትራፊክ ፍሰት በማሻሻል ረገድ አርአያነት ያለውና የተሻለ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን የከተማው ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።

ጣቢያው በተለይም በቁጥጥር፣ በግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብሮች እንዲሁም በትራፊክ ምልክቶችና ማመልከቻዎች ተከላ ላይ በስፋት እየሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል።

የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ የመንገድ ትራፊክ ደኅንነት ዋና ክፍል ኃላፊ ኮማንደር ነገሠ አባተ እንደገለጹት በትራፊክ አደጋ ምክንያት የሚደርሰውን የሕይወት፣ የአካልና የንብረት ጉዳት ለመቀነስ በየደረጃው የሚገኙ የትራፊክ መዋቅሮች ሌሊትና ቀን እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል።

በዚህ ረገድ የ4ኛ ፖሊስ ጣቢያ የትራፊክ ቁጥጥር ክፍል በቁርጠኝነትና በተደራጀ መልኩ እያከናወነ ያለው ተግባር በከተማዋ ያለውን የትራፊክ ደኅንነት ወደተሻለ ደረጃ ያሸጋገረና ለሌሎች ጣቢያዎችም አርአያ የሚሆን ነው ብለዋል።

ኮማንደሩ አክለውም ፖሊስ መምሪያው የጣቢያውን ጠንካራ ተሞክሮ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማስፋፋት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የ4ኛ ፖሊስ ጣቢያ የመንገድ ትራፊክ ደኅንነት ክፍል ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክር አበባው አየለ በበኩላቸው ጣቢያው የሕዝብን ደኅንነት ለመጠበቅና የትራፊክ ሕግ አስከባሪነትን ለማረጋገጥ በሦስት ዋና ዋና ዘርፎች ላይ አተኩሮ መሥራቱን አስረድተዋል።

“በመጀመሪያ ደረጃ፣ አደጋ ሊያሰነሱ በሚችሉ የፍጥነት ማሽከርከር፣ የሰነድ ጉድለትና የቴክኒክ ችግሮች ላይ ጥብቅና ተከታታይነት ያለው የቁጥጥር ሥርዓት ዘርግተናል፤” ያሉት ምክትል ኢንስፔክተሩ፣ ከቁጥጥሩ ጎን ለጎን ለአሽከርካሪዎች፣ ለእግረኞችና ለተማሪዎች ቀጣይነት ያለው የትራፊክ ደኅንነት ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ መከናወኑን ጠቅሰዋል።

ምክትል ኢንስፔክተር አበባው አክለውም ለአደጋ ተጋላጭ በሆኑና ቁልፍ በሆኑ የትራፊክ መጋጠሚያዎች ላይ የትራፊክ ምልክቶችንና የደኅንነት ማመልከቻዎችን የመትከልና የማደስ ሥራ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በስፋት መከናወኑን፤ ይህም አሽከርካሪዎች በቂ መረጃ አግኝተው በኃላፊነት ስሜት እንዲያሽከረክሩ ከፍተኛ እገዛ ማድረጉን ገልጸዋል።

በጣቢያው የቁጥጥር ክልል ውስጥ በዕለት ተዕለት የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ላይ የሚሳተፉ አሽከርካሪዎችም በጣቢያው እየተከናወነ ባለው ተግባር መደሰታቸውን ገልጸዋል።

የአሽከርካሪነት ሙያ ስምሪት ላይ የሚገኘው አሽከርካሪ በታሪክ በቀለ በሰጠው አስተያየት ቀደም ሲል በትራፊክ ምልክቶች እጥረትና በአንዳንድ ሕገ-ወጥ አሽከርካሪዎች ምክንያት ለከፍተኛ አደጋ እንጋለጥ ነበር ሲል ያስታውሳል።

አሁን ግን በ4ኛ ፖሊስ ጣቢያ የትራፊክ ፖሊሶች አማካኝነት የተደረገው የትራፊክ ምልክቶች ተከላና የተጠናከረው የቁጥጥርና የምክር አገልግሎት በራስ መተማመን እንድናሽከረክርና ራሳችንን ከአደጋ እንድንጠብቅ አግዞናል ሲል አሽከርካሪ በታሪክ ምስክርነቱን ሰጥቷል።

የ4ኛ ፖሊስ ጣቢያ የመንገድ ትራፊክ ደኅንነት ክፍል በቀጣይም ከሕብረተሰቡና ከትራንስፖርት ባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ቅንጅት በማጠናከር፣ የሕግ ማስከበርና የአደጋ መከላከል ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ከጣቢያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top