“ከውድመት ወደ ልህቀት!”
የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በሪፎርሙ በመጠቀም ሙሉ አቅሙ መመለሱና የዲግሪ ፕሮግራም ሊጀምር መሆኑ ተገለፀ።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ለረጅም አመታት በኮሌጅነት ያገለገለ አንገፋ ተቋሙ በአማራ ክልል ፖሊስ በተደረገው ሪፎርም ወደ ዩኒቨርሰቲ ኮሌጅነት እንዲሸጋገር ተደርጓል።
ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ በክልሉ ተከስቶ በነበረው ግጭት ሳቢያ ከፍተኛ ውድመት ደርሶበት የነበረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ከተደቀነበት ፈተና ሙሉ በሙሉ አገግሞ መደበኛ ስራውን በብቃት ማከናወን መጀመሩን አስታውቋል።
አሁን ላይ ተቋሙ ጥራት ያለው ትምህርትና ስልጠና ለመስጠት፣ ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር ለማካሄድ እንዲሁም የማህበረሰብ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የተጣለበትን ሀገራዊና ክልላዊ ተልዕኮ ለማሳካት በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፕሬዝዳንት ምክትል ኮሚሽነር አበበ ደለለ እንደገለጹት ተቋሙ በ1985 ዓ.ም ታህሳስ ወር ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ መሰረታዊ የፖሊስ ስልጠናን ጨምሮ ለአመራሮችና ለተለያዩ የፖሊስ መዋቅሮች ልዩ ልዩ ሙያዊ ስልጠናዎችን ሲሰጥ የቆየ አንጋፋ ተቋም ነው ብለዋል።
ከኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በመቀጠል በታሪካዊነቱና በትልቅነቱ የሚጠቀሰው ይህ ተቋም ለአማራ ክልል ብቻ ሳይሆን ለሌሎች እህት ክልሎች ጭምር በርካታ የፖሊስ ሰራዊትን አቅም ሲገነባ መቆየቱን አስታውሰዋል።
ይህ ተቋም በአጭር ጊዜ ውስጥ አገግሞ ወደ ሙሉ ስራው እንዲመለስ የክልሉ መንግስት፣ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ እንዲሁም የተለያዩ የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ያደረጉት ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን የዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ፕሬዝዳንት አብራርተዋል።
በክልሉ መንግስት ምክር ቤት በይፋ ጸድቆ ወደ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅነት ያደገው ተቋሙ የፖሊስ ሰራዊቱን የእውቀትና የክህሎት አድማስ ይበልጥ ለማስፋት አዲስ ምዕራፍ ሊጀምር መሆኑ ተበስሯል።
በዚህም መሠረት በወንጀል መከላከል (Crime Prevention) የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርት ለመጀመር የሚያስችሉ ሁሉንም አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶች በአስተማማኝ ሁኔታ ማጠናቀቁን ምክትል ኮሚሽነር አበበ ደለለ ይፋ አድርገዋል።
ይህንን የዲግሪ ፕሮግራም ውጤታማ ለማድረግም በክልሉ ከሚገኙ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የጠበቀ አጋርነት መፈጠሩን ጠቅሰው፤ በተለይም የመምህራንን አቅም በማሳደግና በቁሳቁስ ድጋፍ ዙሪያ በጋራና በትብብር እየተሰራ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።
“በተደረገልን ሁለንተናዊ ድጋፍና እገዛ በአሁኑ ወቅት ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ በተሟላ አቅሙ ስልጠና መስጠት በሚችልበት የላቀ ደረጃ ላይ ይገኛል” ሲሉ ምክትል ኮሚሽነር አበበ ደለለ አጽንኦት ሰጥዋል።
በክልሉ በነበረው ግጭት ምክንያት በዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ላይ የደረሰው ውድመት በትምህርትና ስልጠናው ሂደት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሮ እንደነበር የአካዳሚክስ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ግዛቸው ከበደ ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ይህንን ፈታኝ ወቅት በጽናት በማለፍ፣ ከውድመቱ ማግስት ጀምሮ መደበኛ የፖሊስ ስልጠናዎችን ጨምሮ ልዩ ልዩ ሙያዊ ስልጠናዎች ሳይቋረጡ እንዲሰጡ ተደርጓል።
በተለይም በክልሉ የፖሊስ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰጠውን የማዕረግ ሽግግር ስልጠና በስኬት ማጠናቀቅ መቻሉ የተቋሙን ጠንካራ የመልሶ ማገገም አቅም ያሳየ እንደነበር ተገልጿል።
ረዳት ኮሚሽነር ሙሉጌታ ዳኜ የተቋሙ የሰው ኃይል እና ፋይናንስ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት በበኩላቸው ለስልጠናው ሂደት ስኬታማነት እጅግ አስፈላጊ የሆኑ የቁሳቁስና የሎጂስቲክስ ግብዓቶች በየደረጃው እየተሟሉ በመሆናቸው፣ ተቋሙ የጀመረውን የትምህርትና ስልጠና ተልዕኮ በሙሉ አቅሙና በጥራት ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የፖሊስ ዩኒቨርሲቲው የጥናትና ምርምር ሥርዓተ-ትምህርት ዋና መምሪያ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር መላኩ ሲሳይ እንደገለጹት ተቋሙ ከመደበኛ ስልጠና ባለፈ የክልሉን ህዝብ ዘላቂ ሰላምና ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ማረጋገጥ የሚያስችሉ ሳይንሳዊና ችግር ፈቺ ጥናቶች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው።
በሰላምና ጸጥታ ዙሪያ የሚታዩ ክፍተቶችን በጥናት በመለየት ተግባራዊ መፍትሄዎችን የማቅረብ ስራ በስፋት እየተከናወነ ይገኛል ሲሉ አብራርተዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ በፖሊሳዊ ሳይንስና በሰላም ግንባታ ዙሪያ ያከናወናቸውን ጥናቶች ለህዝብና ለፖሊሲ አውጭዎች የሚያቀርብበትንና በሰፊው የሚወያይበትን 4ኛውን የጥናትና ምርምር ሲምፖዚየም ለመጪው ግንቦት 20 እና 21 ቀን 2018 ዓ.ም ለማካሄድ ዝግጅቱን በሙሉ አቅሙ ማጠናቀቁን ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ፕሬዝዳንት ምክትል ኮሚሽነር አበበ ደለለ መልዕክታቸውን ሲያጠቃልሉ፤ ለአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጀኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር) እና ለጠቅላይ መምሪያው ማኔጅመንት አባላት ልዩ ምስጋና አቅርበዋል።
አመራሩ ተቋሙ ከደረሰበት ውድመት እንዲያገግም፣ አደረጃጀቱ እንዲዘምንና ወደ ላቀ የልህቀት ደረጃ እንዲሸጋገር ሌላው ቀርቶ ለዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ በልዩ ሁኔታ ከፍተኛና ተከታታይነት ያለው ድጋፍ በማድረግ ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በመጨረሻም የተቋሙን የመልሶ ግንባታ ስራዎች ይበልጥ ለማጠናከርና ለትምህርትና ስልጠናው ሂደት የሚያስፈልጉ ዘመናዊ ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችን በአይነትም ሆነ በገንዘብ ለመደገፍ የተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የልማት አጋሮች እንዲሁም ባለሀብቶች የበኩላቸውን አሻራ እንዲያኖሩ የአማራ ክልል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ አመራሮች ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።









