በአዊ ብሔረሰብ ዞን የግዳጅ አፈጻጸምና የ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የጸጥታ ዝግጅት ተገመገመ
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ስትራቴጂክ አመራሮች በተገኙበት በአዊ ዞን ስር የሚገኙ የጸጥታ መዋቅሮች የግዳጅ አፈጻጸምና የመጪው 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ተልዕኮ አፈጻጸም ላይ ያተኮረ ጥልቅ ግምገማዊ ውይይት ተካሄደ።
በመድረኩ ላይ የእንጅባራ ከተማና የባንጃ ወረዳ ፖሊስ፣ የ39ኛ አድማ መከላከል ሻለቃ እና የሰላም አስከባሪ ሚሊሻ አመራርና አባላት የተሳተፉ ሲሆን ውይይቱን የክልሉ ፖሊስ ስትራቴጂክ አመራሮች በጋራ መርተውታል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነርና የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር አበበ ውቤ ፤ የጸጥታ መዋቅሩ ቀጠናውን ከጠላት በመከላከል ረገድ ላሳየው ተጋድሎ እውቅና የሰጡ ሲሆን፣ የታዩ የቁርጠኝነት ክፍተቶችንና ተቋማዊ ፈተና የሆነውን ክህደትን በጽናት መታገል እንደሚገባ አሳስበዋል።
መጪው ምርጫ ያለ ምንም የጸጥታ ስጋት እንዲከናወንም ጥሪ አቅርበዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነርና የአስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ረዳት ኮሚሽነር አያልነህ ተስፋዬ በፖሊሳዊ ሪፎርምና በዲሲፕሊን ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ የህግ ማስከበር ስራው ከምንጊዜውም በላይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
ኮሎኔል አበበ አደመ የመከላከያ ሰራዊት ምስራቅ ዕዝ ክፍለ ጦር አዛዥ በበኩላቸው ሰራዊቱ ግዳጅን በጀግንነትና በቁርጠኝነት ከፈጸመ የማይመክተው ጠላት እንደሌለ ገልጸው፣ በምርጫው ወቅት ሊወሰዱ ስለሚገቡ የጸጥታ ጥንቃቄዎች አቅጣጫ አስቀምጠዋል።



