“የአማራን ህዝብ ሰላም ለማስጠበቅና ጠላቶቹን አደብ ለማስገዛት ሁሌም ዝግጁ ነን!!” የ36ኛ ሻለቃ የአድማ መከላከል ሠራዊት

“የአማራን ህዝብ ሰላም ለማስጠበቅና ጠላቶቹን አደብ ለማስገዛት ሁሌም ዝግጁ ነን!!” የ36ኛ ሻለቃ የአድማ መከላከል ሠራዊት

የአማራ ክልል ፖሊስ የ36ኛ ሻለቃ የአድማ መከላከል ሠራዊት አባላት ሥነ-ልቦናዊና አካላዊ ዝግጁነታቸውን በመጠበቅ ማንኛውንም የላቀ ወታደራዊ ግዳጅ በብቃት ለመፈፀም ሁሌም ዝግጁ መሆናቸውን ገለጹ።

ሠራዊቱ በተሰማራበት የግዳጅ ቀጠና ሁሉ ሕገ-ወጥ ታጣቂ ቡድኑን በመደምሰስ የአካባቢውን ሰላም የማስፈን ተልዕኮውን በድል አድራጊነት መወጣቱን አስታውቋል።

የአማራን ሕዝብ ዕረፍት ለመንሳትና ኢትዮጵያን ለማተራመስ የሚዳዳቸውን ታሪካዊ ጠላቶችም ሆኑ በሀገር ውስጥ የተፈለፈሉ የጥቅም አደሮችን አደብ ለማስገዛት ሠራዊቱ የሚሰጠውን ማንኛውንም ግዳጅ የመፈፀም ሙሉ ብቃትና ቁርጠኝነት እንዳለው አባላቱ አረጋግጠዋል።

የ36ኛ ሻለቃ አዛዥ ምክትል ኮማንደር በሪሁን ውዱ በበኩላቸው “ጀግንነትን ተላብሰን፣ ፈተናዎችን በጽናት ተጋፍጠን፣ የአማራን ህዝብ ከማንኛውም ጥቃት እየጠበቅን እንገኛለን፤ የሚሰነዘርብንንም ጥቃት በመመከት የክልላችን እና ሀገራችንን ሰላም ለማስፈን ግዳጃችንን በጀግንነት እየተወጣን ነው” ብለዋል።

የሚሰጣቸውን ግዳጅ በእውቀትና በጥበብ ለመፈፀም በአካልም ሆነ በሥነ-ልቦና ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹት አዛዡ፣ ሻለቃው ጠላትን አምርሮ የሚጠላና በተሰማራበት የውጊያ ቀጠና ሁሉ ውጤታማ መሆኑን አስረድተዋል።

እንደ አዛዡ ገለጻ ደብረ ማርቆስ ከተማን መነሻ በማድረግ በተለያዩ አካባቢዎች በተከናወነ ኦፕሬሽን በርካታ የታጠቁ ኃይሎች እጃቸውን እንዲሰጡ ተደርጓል። ጠላት ይዟቸው የነበሩ ቦታዎችን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር የሕዝብ ሰላም እንዲረጋገጥ ተደርጓል።

የሻለቃው ወታደራዊ ወትሮ ዝግጁነት እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ በጠላት ላይ በርካታ ድሎችን መጎናጸፍ ተችሏል ሲሉ አዛዡ አብራርተዋል።

ምክትል ኮማንደር በሪሁን አክለውም የኦፕሬሽን ሥራዎች በሙሉ ፍፁም ፖሊሳዊ ሥነ-ምግባርን በተላበሰ መልኩ እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሠራዊቱ ወታደራዊ ተልዕኮውን ከመወጣት ባለፈ በተሰማራባቸው አካባቢዎች ሁሉ የደረሱ ሰብሎችን በመሰብሰብና የአቅመ-ደካሞችን ቤት በማደስ ሕዝባዊነቱን በተግባር አሳይቷል ብለዋል።

በዚህም ምክንያት ኅብረተሰቡ ለሠራዊቱ ወሳኝ መረጃዎችን በመስጠትና አጋዥ በመሆን አብሮ እየሠራ ይገኛል።

በዚህ የተቀናጀ ጥረት በተፈጠረው አንጻራዊ ሰላም ለሕብረተሰቡ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት መደበኛ ሥራቸውን በነፃነት ማከናወን መጀመራቸውን ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በክልሉ የጀመረውን ‘የጀግኖች ማዕከል’ ግንባታ ፕሮጀክት የ36ኛ ሻለቃ አዛዥና አባላት በከፍተኛ ደስታ እንደተቀበሉት ገልጸዋል።

ይህ ግንባታ ለፖሊስ ሠራዊቱ የተሰጠ ትልቅ የታሪክ አሻራ መሆኑን በመጥቀስ ተዋጊ ኃይሉ ለግንባታው መሳካት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

በመጨረሻም የሻለቃው አባል የሆኑት ዋና ሳጅን መኳንንት አዲሴ እና የድሽቃ ተኳሹ ሳጅን ብርሃኑ ዓለምነህ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለማስጠበቅ ከአጋር የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን በርካታ ስኬታማ ሥራዎችን እያከናወኑ መሆኑንና ይህንኑ ተጋድሎ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በቁርጠኝነት ገልጸዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top