“በደብረ ማርቆስ ለሰንደቅ ዓላማ የሚሰጠው ፖሊሳዊ ክብር!”
በደብረ ማርቆስ ከተማ በፖሊሳዊ ሥነ-ሥርዓት ሰንደቅ ዓላማ የማውጣትና የማውረድ መርሃ-ግብር በይፋ ተጀመረ
የሰንደቅ ዓላማን ክብርና የሀገርን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ እንዲሁም የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የጀመረውን ሪፎርም ተከትሎ፣ በደብረ ማርቆስ ከተማ በንጉሥ ተክለ ሃይማኖት አደባባይ ጠዋትና ማታ በፖሊሳዊ ሥነ-ሥርዓት ሰንደቅ ዓላማ የማውጣትና የማውረድ መርሃ-ግብር በይፋ ተጀምሯል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ የክብር ዘቦችን፣ ግራና ቀኝ የሚያጅቡ እንዲሁም ሰንደቅ ዓላማውን የሚያወጡና የሚያወርዱ የፖሊስ አባላትን በክብር በማሰማራት ሥነ-ሥርዓቱን ያለማቋረጥ ማከናወን ጀምሯል።
በዚህ ሥነ-ሥርዓት ወቅት የፖሊስ ፊሽካ በሚነፋበት ጊዜ እግረኛም ሆነ ተሽከርካሪ ባለበት በመቆም ለሰንደቅ ዓላማው የሚገባውን ክብር እንደሚሰጡ ታውቋል።
የማስጀመሪያ ፕሮግራሙን በይፋ የከፈቱት የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ተሾመ ዋለ ባደረጉት ንግግር ሰንደቅ ዓላማ ለአንድ ሀገር ከፍተኛ ትርጉም ያለው የሉዓላዊነት መገለጫ በመሆኑ በሕዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ጠዋትና ማታ መከበሩ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
በተለይም ለመለዮ ለባሹ የሕይወት መሥዋዕትነት የሚከፈልለት በመሆኑ ልዩ ክብር እንደሚሰጠው ገልጸዋል።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አክለውም በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የተጀመረው አዲሱ ሪፎርም በከተማ አስተዳደርና በጣቢያ ደረጃ እያሳየ ያለው የለውጥ ጅማሮ አበረታች በመሆኑ ይበልጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አመልክተዋል።
የፖሊስ ዋና ሥራ የሕዝብን ሰላም ከሕዝብ ጋር በመሆን ማስከበርና ወንጀልን መከላከል መሆኑን የጠቀሱት አቶ ተሾመ የደብረማርቆስ ከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ ሰላምን ለማስከበር ለሚያደርጋቸው ጥረቶች ሁሉ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
በተጨማሪም የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ የክብር ዘቦች የደብረ ማርቆስ አየር መንገድ የመጀመሪያ የሙከራ በረራውን ባደረገበት ወቅት ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ለአቶ አረጋ ከበደና ለልዑካን ቡድናቸው ላደረጉት ደማቅ የክብር አቀባበል ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል።
ለነዚህ የክብር ዘቦችና ለሰንደቅ ዓላማ ሥነ-ሥርዓቱ አስፈጻሚዎች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።
በዚህ የማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ላይ የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ተሾመ ዋለ፣ የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ቢምረው አሰፋ፣ እንዲሁም የመምሪያውና የአራቱ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ አመራሮችና አባላት ተገኝተዋል።







