የስትራቴጂካዊቷ ደጀን ከተማ ዘላቂ ሰላም በጋራ ቅንጅት መረጋገጡ ተገለጠ።

የስትራቴጂካዊቷ ደጀን ከተማ ዘላቂ ሰላም በጋራ ቅንጅት መረጋገጡ ተገለጠ።

በምስራቅ ጎጃም ዞን የደጀን ከተማ ህብረተሰቡና ፖሊስ በቅንጅት በመስራታቸው በአሁኑ ወቅት ሙሉ የሰላም አየር እየተነፈሰች መሆኑን የከተማዋ ፖሊስ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

ደጀን ከተማ ከአማራ ክልል ወደ ዋና ከተማዋ አዲስ አበባ በሚወስደው ዋና መስመር ላይ የምትገኝ ስትሆን፣ ከፍተኛ የተሽከርካሪ ፍሰት የሚስተናገድባትና በከፍተኛ ፍጥነት እያደገች የመጣች የኢንዱስትሪ ከተማ ናት።

ይህንን ስልታዊ መልክዓ-ምድራዊ ጠቀሜታዋን ከግምት ውስጥ በማስገባት አጠቃላይ የከተማዋን ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ።

የከተማዋ ፖሊስ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ ከፌደራል ፖሊስ፣ ከአጎራባች ክልሎችና ከአጋር የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የጋራ ከፍተኛ የጸጥታና የደህንነት ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል። ይህ የጋራ ጥረትም በከተማዋ ላይ አስተማማኝ መረጋጋትና ተጨባጭ ውጤት እንዲመዘገብ አስችሏል።

የደጀን ከተማ ፖሊስ ጽህፈት ቤት አዛዥ ኢንስፔክተር አውራሪስ ከበደ እንደገለጹት በከተማዋ የተመዘገበው አመርቂ የሰላም ውጤት የመነጨው በፖሊስና በህዝቡ መካከል ካለው ጠንካራ መተማመንና ቅንጅታዊ አሰራር ነው።

ከተማዋን የሰላም ቀጠና ለማድረግ ‘የሰላሜ ዘብ እኔው ነኝ’ በሚል መርህ ህብረተሰቡን በየሰፈሩ በማደራጀት ጭምር ወደ ስራ መገባቱን አዛዡ አስረድተዋል።

ኢንስፔክተር አውራሪስ አክለውም “ፖሊስ ብቻውን ሰላምን ማስፈን አይችልም። የደጀን ከተማ ህዝብ ግን ይህንን ተረድቶ መረጃ በመስጠት እና በፓትሮል (የጥበቃ) ስራው ላይ በቀጥታ በመሳተፍ፣ ወንጀለኞችና የሰላም ጠላቶች የሚንቀሳቀሱበትን ቀዳዳ በሙሉ እንዲዘጋ አድርጓል” ብለዋል።

በከተማዋ የ01 ቀበሌ የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ባለሙያ ዋና ሳጅን መብራቴ ተክለ ወልድ በሰጠው አስተያየት “ከህዝቡ የምናገኘው ድጋፍ ለስራችን ትልቅ አቅም ሆኖናል። ህብረተሰቡ አጠራጣሪ ነገሮችን በፍጥነት ለጸጥታ አካላት ያሳውቃል፤ አብሮንም ያድራል፤ ይህም የወንጀል ስጋትን አስቀድሞ ለመከላከል አስችሎናል” ብሏል።

የከተማዋ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ አታለለች ወርቁ እና አቶ ምስጋናው ሁነኛው በሰጡት አስተያየት “ከተማችን የንግድና የትራንስፖርት መነሻና መድረሻ በመሆኗ ሰላሟ መረጋገጡ ለእኛ ለነዋሪዎቹም ሆነ ለልማታችን ትልቅ ትርጉም አለው። ‘የሰላሜ ዘብ እኔው ነኝ’ ብለን በየሰፈራችን መደራጀታችንና ከፖሊስ ጋር በቅንጅት መስራታችን ሰላማችንን በባለቤትነት እንድንጠብቅ አድርጎናል” ሲሉ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በደጀን ከተማ የህዝብ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ፣ የንግድና የኢንዱስትሪ ስራዎች እንዲሁም የትራንስፖርት ፍሰቱ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ እየተከናወነ እንደሚገኝ የከተማዋ ፖሊስ ጽህፈት ቤት አረጋግጧል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top