“የጸጥታ አካላት ቅንጅት እና የህዝብ ደኅንነት በምስራቅ ጎጃም”

“የጸጥታ አካላት ቅንጅት እና የህዝብ ደኅንነት በምስራቅ ጎጃም”

በምስራቅ ጎጃም ዞን አስተማማኝ ሰላም መስፈኑን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ

በምስራቅ ጎጃም ዞን ላለፉት ወራት የህዝቡን ደኅንነት እና የዜጎችን ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለማረጋገጥ በተከናወነ የተቀናጀ የወንጀል መከላከል ስራ በአሁኑ ወቅት በዞኑ አስተማማኝ ሰላም መስፈኑን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ገለጸ።

የምስራቅ ጎጃም ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ግርማ ጫኔ እንደገለጹት፤ በዞኑ የነበሩ የጸጥታ ስጋቶችን በዘላቂነት ለመፍታት የዞኑ ፖሊስ ሰራዊት ከመከላከያ ሰራዊት፣ ከፌደራል ፖሊስ እና ከሌሎች የጸጥታ አካላት በጋራ በመሥራታቸው ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል።

ኮማንደር ግርማ አክለውም “የህዝብ እርካታ የሙያዊ ስኬታችን መገለጫ ነው!” በሚል መሪ ቃል አስቸጋሪ መልክዓ ምድራዊና የአየር ንብረት ሁኔታዎችን ተቋቁሞ የጸጥታ ኃይሉ ባከናወነው ኦፕሬሽን በአካባቢው ተጋርጦ የነበረው የጸጥታ ስጋት ተቀልብሷል፤ የዜጎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ወደ ቀድሞ ሁኔታው ተመልሷል፤ ህዝቡ ያለምንም ስጋት መደበኛ ተግባሩን እንዲያከናውን ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል።

የዞኑ ፖሊስ የወንጀል መከላከል ምክትል መምሪያ አዛዥ ኮማንደር አምሳል ሰውነት በበኩላቸው ዞኑ ቀደም ሲል በህገወጥ ታጣቂ ቡድኖች ከፍተኛ ውድመትና ዘረፋ ይፈጸምበት እንደነበር አስታውሰዋል። ሆኖም በአሁኑ ወቅት ሰላሙን ዘላቂ ለማድረግ ማህበረሰቡ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ኮማንደር አምሳል ገለጻ ማህበረሰቡ በፓትሮል ስራ እና መረጃ በመስጠት ከፖሊስ ጎን በመቆሙ፣ ከሀይማኖት አባቶች እና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በቅንጅት መስራት መጀመሩ በዞኑ ለተገኘው አንጻራዊ ሰላም እና ለውጤታማነቱ በምክንያትነት ጠቅሰዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ሪፎርምን ተከትሎ በዞኑ ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን የገለጹት የሰው ኃይል ልማት አስተዳደር ምክትል መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ማስተዋል ዘሪሁን ናቸው።

እንደ አዛዧ ገለጻ “ይህ ሪፎርም ሙያና ሙያተኛን ያገናኘ፣ ፖሊስ ወደ ቀደመ ክብሩ እንዲመለስ ያደረገ እና ተቋሙ ገለልተኛ ሆኖ አገልግሎት እንዲሰጥ ያስቻለ ነው።”

ሰራዊቱ ሙያዊ ስነ-ምግባርን ተላብሶ ዜጎችን እንዲያገለግል ተከታታይ የሆኑ የስብዕና ግንባታ ስልጠናዎች እየተሰጡ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

በክልሉ ፖሊስ ውስጥ እየተተገበሩ ያሉ የሪፎርም እና የለውጥ ስራዎች አባላቱ በቁርጠኝነትና በተነሳሽነት ግልጋሎት እንዲሰጡ ምቹ ሁኔታን ፈጥረዋል። ይህም የፖሊስ ሰራዊቱን ሙያዊ ብቃትና ተቋማዊ አቅም ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተለይም በዋና ጠቅላይ መምሪያው አማካኝነት ግንባታው የተጀመረውን የጀግኖች ማዕከል ፕሮጀክትን በተመለከተ አስተያየታቸውን የሰጡት አባላቱ፤ “ማዕከሉ ለሀገርና ለህዝብ ሰላምና ደህንነት ሲሉ መስዋዕትነት ለከፈሉ የፖሊስ አባላት የሚሰጠውን ክብርና ትኩረት የሚያሳይ በመሆኑ እጅግ አስደስቶናል” ሲሉ ያነጋገርናቸው የሰራዊቱ አመራሮች እና አባላት ተናግረዋል።

በመጨረሻም፣ በምስራቅ ጎጃም ዞን የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም ወደ አስተማማኝና ዘላቂ ደረጃ ለማሸጋገር የፖሊስ ኃይሉ የወንጀል መከላከልና የተቀናጀ የኦፕሬሽን ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top