በህገ-ወጥ የነዳጅ ዝውውርና የትራንስፖርት ታሪፍ ጭማሪ ላይ የተጠናከረ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑ ተገለጸ

በህገ-ወጥ የነዳጅ ዝውውርና የትራንስፖርት ታሪፍ ጭማሪ ላይ የተጠናከረ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑ ተገለጸ

በአማራ ክልል ህገ-ወጥ የነዳጅ ዝውውር እና ሽያጭ እየጨመረ በመምጣቱ፣ የተደራጀ የጋራ ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ የተጠናከረ የህግ ማስከበር ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አስታውቋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የትራፊክ ቁጥጥር ደህንነት ዋና መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር በቀለ አብዬ እንደገለጹት፤የአለም አቀፍ የነዳጅ እጥረትን ተከትሎ በክልሉ የሚስተዋሉ ህገ-ወጥ ተግባራትን ለመቆጣጠር ከፍተኛ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገልጸዋል።

በነዳጅ እጥረት ሰበብ በርካታ የማህበረሰብ ክፍል ለከፍተኛ እንግልት ተዳርጎ የነበረ ቢሆንም ከክልል እስከ ወረዳ የሰው ኃይል በማዋቀር ችግሩን መፍታት ተችሏል ብለዋል።

ይሁን እንጂ አንዳንድ አሽከርካሪዎች ነዳጅ ከቀዱ በኋላ ወደ ስራ ከመግባት ይልቅ ነዳጁን በህገ-ወጥ መንገድ የመሸጥ ድርጊት እየፈጸሙ በመሆኑ ከድርጊታቸው ሊታቀቡ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የነዳጅ እጥረትን ሰበብ በማድረግ ትርፍ በጫኑና ታሪፍ በጨመሩ 4 ሺህ 625 አሽከርካሪዎች ላይ የተቀናጀ እርምጃ የተወሰደ ሲሆን፣ በታሪፍ ጭማሪ ምክንያት ከአሽከርካሪዎች ለ26 ሺ 910 ተሳፋሪዎች ገንዘባቸው እንዲመለስ ተደርጓል።

እንዲሁም ትርፍ በጫኑ አሽከርካሪዎች ላይ ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ

የገንዘብ ቅጣት ተጥሎባቸዋል።

ኮማንደር በቀለ አብዬ አክለውም፣ የጸጥታ ኃይሉ ከህብረተሰቡ ጋር ያለው ቅንጅት ጠንካራ በመሆኑ ስለ ህገ-ወጥ አካላት ሙሉ መረጃ እየተገኘ ክትትል እየተደረገባቸውና ለህግና ስርዓት ተገዢ እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የነዳጅ እጥረቱ ወደ ትክክለኛው ደረጃ እስኪመለስ ድረስ ክትትሉና ቅጣቱ በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

በየኬላውና በየምድቡ የሚገኙ ህግ አስከባሪዎችና የትራፊክ ባለሙያዎች ወጥ የሆነ የህግ ማስከበር ተግባር ማከናወን እንዳለባቸው አሳስበው፤ አሁን ላይ የነዳጅ እጥረቱ እየተስተካከለና ቁጥጥሩ እየጠነከረ በመሆኑ ህገ-ወጥ ተግባር የሚፈጽሙ አካላት ከወዲሁ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡና ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ለሀገር እድገትና ለህዝብ የተረጋጋ ህይወት ሁሉም አካል በኃላፊነት ስሜት መስራት እንዳለበትም አጽንኦት ሰጥተዋል።

የክልሉ ፍትህ ቢሮ የኢኮኖሚ ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ አሻግሬ እንደገለጹት፤ መንግስት ነዳጅን በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬና ገንዘብ ወደ ሀገር ውስጥ የሚያስገባ በመሆኑ በአቅርቦት በኩል ምንም ዓይነት እጥረት እንደሌለ ገልጸው አሁን ለሚታየው ችግር ዋነኛ ምክንያቶቹ ህገ-ወጥ ዝውውርና ህገ-ወጥ ሽያጭ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።

በተለይም አንዳንድ ማደያዎች ከህገ-ወጥ አካላት ጋር በመመሳጠር ነዳጅ በጥቁር ገበያ እየሸጡ መሆኑንና በመኪና ላይ ተጨማሪ ሳልባትዮ ማስገጠም፣ በጀሪካን መቅዳት እና የነዳጅ ግብይት በዲጂታል መንገድ መሆኑ እየታወቀ በህገ-ወጥ ደላሎች አማካኝነት መሸጥ በአስቸኳይ መቆም እንዳለበት አሳስበዋል።

ይህን ችግር ለመቅረፍ ከየካቲት 23/2018 ዓ.ም ጀምሮ ከክልል እስከ ወረዳ የተዋቀረው የጋራ ግብረ-ኃይል ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ለይቶ ወደ ስራ መግባቱን አቶ ሙሉጌታ አብራርተዋል።

በዚህም መሰረት እስካሁን በተደረገ ክትትልና ምርመራ በህገ-ወጥ ተግባር ላይ የተሳተፉ 170 የሚሆኑ ሰዎች የተያዙ ሲሆን፣ 115 የክስ መዝገቦች ተጣርቶ ለአቃቢ ህግ መላኩን ጠቁመው 17 የሚሆኑ ግለሰቦች ላይ ከገንዘብ እስከ 7 ዓመት እስራት መፈረዱን ገልጸዋል።

በተጨማሪም 33 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ህገ-ወጥ ነዳጅ ተይዞ ወደ መንግስት ገቢ ተደርጓል።

ይህ ህገ-ወጥ ተግባር በሀገሪቱ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና ማህበራዊ ህይወት ላይ ከፍተኛ ጫና የሚያደርስ በመሆኑ፣ ህብረተሰቡ ከፍተኛ ክትትል እንዲያደርግና ህገ-ወጥ አካላትን አሳልፎ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል።

በዚህ ተግባር ላይ የተሰማሩ አካላት ንብረታቸው ከመወረሱ ባሻገር በህግ በጥብቅ እንደሚጠየቁ አውቀው ጥንቃቄ እንዲያደርጉና የተደራጀው ግብረ-ኃይልም ህግ የማስከበር ኃላፊነቱን በተገቢው መንገድ እንዲወጣ አሳስበዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top