የጸጥታ ኃይሉን ግዳጅ አፈጻጸምን ይበልጥ ለማጠናከርና ቀጣይ የሰላም ስራዎችን በላቀ ዝግጁነት ለመምራት የሚያስችል የአቅም ግንባታና የውይይት መድረክ ተካሄደ።

የጸጥታ ኃይሉን ግዳጅ አፈጻጸምን ይበልጥ ለማጠናከርና ቀጣይ የሰላም ስራዎችን በላቀ ዝግጁነት ለመምራት የሚያስችል የአቅም ግንባታና የውይይት መድረክ ተካሄደ።

መድረኩ የአማራ ክልል የፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ባዘጋጀዉ የስራ ላይ የአቅም ግንባታ ስልጠና መድረክ ቀጣይ ክፍል ሲሆን ፣ የጸጥታ ኃይሉን ስምሪትና ውጤታማነት ለማሳደግ ያለመ ነው።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ስትራቴጂክ እና ከፍተኛ አመራሮች ከባህርዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ፣ ከሰሜን ጎጃም ዞን ፖሊስ መምሪያ፣ከቪ አይ ፒ፣ከ1ኛ ሻለቃ አድማ መከላከል ፖሊስ እና የልዩ ተቋማትና መሰረተ ልማት ጥበቃ ፖሊስ አመራሮችና አባላት ጋር በጸጥታ ኃይሉ የግዳጅ አፈጻጸም የአቅም ግንባታ የስራ ላይ ዉይይት ዙሪያ በባህርዳር አካሂደዋል።

በመድረኩም መነሻ ሰነድ ላይና ፣እስካሁን የተከናወኑ የጸጥታ ስራዎች በዝርዝር የተገመገሙ ሲሆን፣ በቀጣይም በክልሉ አስተማማኝ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚያስችሉ የግዳጅ አፈጻጸም ስልቶች ላይ ውይይት ተደርጓል።

በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነርና የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር አበበ ውቤ እንደተናገሩት፤ በባህርዳር ከተማና አካባቢዋ የተሰሩ ሁሉን ዓቀፍ የወንጀል መከላከል እና ህግ የማስከበር ስራዎች የተሻለ ውጤት ተመዝግበዋል ብለዋል።

በፀጥታ ሀይሉ ውስጥ የሚስተዋሉ የስነምግባርና ሌሎች ችግሮችን በመቅረፍ የማህበረሰባችንን የሰላምና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት በተሰጠን ታላቅ ሙያ ልክ ማገልገል እንደሚገባም አሳስበዋል።

የቪ አይ ፒ እና ተቋም ጥበቃ ሰራዊታችን የተሻለ የእጀባ፣የመሰረት ልማት እና ልዩ ልዩ ተቋማት ጥበቃ ስራን በመስራት አመርቂ ውጤት አምጥቷል ሲሉም ምክትል ኮሚሽነር አበበ ውቤ አክለዋል።

አዛዡ አያይዘውም ፖሊስ ሰራዊታችን ከመደበኛ ተግባሩ ባሻገር በህግ ማስከበር ስራ ተሰማርቶ የህይወት መስዕዋትነትን በመክፈል ህዝባዊ ወገንተኝነቱን እያረጋገጠ ይገኛል።

ባህርዳር ከተማ አስተዳደር በርካታ ክልላዊ፣ሀገራዊና ዓለማቀፋዊ ሁነቶችን ያለምንም የፀጥታ ስጋት ያስተናገደችው በከተማዋ የፀጥታ ሀይል እና ማህበረሰብ የጋራ ጥረት መሆኑንም ምክትል ኮሚሽነሩ አመላክተዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነርና የአስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ረዳት ኮሚሽነር አያልነህ ተስፋዬ በበኩላቸው ፤ የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ እንደ ሌሎች ዞኖች ሁሉ ለክልሉ ሰላም መጠበቅ ትልቅ ዋጋ በመክፈል ከተማዋን የተሻለ ሰላም እንዲኖራት አድርጓል ብለዋል።

እንደ ረዳት ኮሚሽነር አያልነህ ተስፋዬ ገለጻ፤ በክልሉ ፖሊስ ተቋም የተሰራው የሪፎርም ስራ ተቋምን እንዲቀይር፣ሙያን እንዲያጎለብት እና ህዝብን እንዲጠቅም ታስቦ የተሰራ በመሆኑ ይህን የሚመጥን ስራን መስራት ይጠበቃል ሲሉ አፅንኦት ሰጥተዋል።

ረዳት ኮሚሽነር አያልነህ ተስፋዬ አያይዘውም የስራ ውጤታማነት የሚለካው በምናገለግለው ማህበረሰብ እርካታ ልክ በመሆኑ የማህበረሰባችንን መብት፣ሰላም፣ክብርና እሴት ማክበር የፖሊስ መለያ ሊሆን ይገባል።

የቪ አይ ፒ እና ተቋም ጥበቃ ፖሊስ ሰራዊቱ ከተሰጠው መደበኛ ሀላፊነት ባሻገር የህግ ማስከበር ስራ እየሰራ ውጤት እያስመዘገበ ያለ የአላማ ፅናትንና የህዝብ አገልጋይነትን ማሳያ ነው።

7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ያለምንም የፀጥታ ስጋትና ሁከት እንዲጠናቀቅ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በጥምረትና በትኩረት በመስራት የተጣለብንን ትልቅ ሙያዊ እና ተቋማዊ ኀላፊነት መወጣት ይጠበቃል ሲሉም አሳስበዋል።

የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው በበኩላቸው፤ በበጀት ዓመቱ የከተማዋን ሰላም ለማረጋገጥና የተረጋጋ ማህበረሰብ እንዲኖር ለማድረግ በተሰሩ የፀጥታ ማስፈንና የወንጀል መከላከል ስራ ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል።

የእገታና ዝርፊያ ወንጀሎች ከባለፈው በጀት ዓመት አንፃር ሲታይ መቀነሱን የጠቆሙት ኮማንደር ዋለልኝ ችግሩን በትኩረት በማየት ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ቁርጠኛ መሆን የቀጣይ አንዱ ተግባራችን ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።

ከተቋማዊ ሪፎርም አፈፃፀም አንፃርም ፖሊስ መምሪያውን የሚመጥን የቢሮ ግንባታ እየተገነባ ሲሆን በሰው ሀይል ምደባው በኩልም ሙያና ሙያተኛን ያማከለ ስራ ሰለመሰራቱም አመላክተዋል።

የሰሜን ጎጃም ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር በሪሁን አየነው፤ የዞኑ ፖሊስ ሰራዊት ከመደበኛ ተግባሩ ባሻገር ከሌሎች የክልልና የፌደራል የፀጥታ አካላት ጋር በጋራ በመሆን በዞኑ በርካታ አካባቢዎች ላይ ባደረገው ጠንካራ የህግ ማስከበር ስራ በህገ-ወጥ ሀይሉ ተይዘው የነበሩ ቀጠናዎችን ነፃ በማድረግ አንፃራዊ ሰላም ማምጣት ተችሏል ብለዋል።

የ1ኛ ሻለቃ አድማ መከላከል ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር አስማማው ብርሀኔ፤ ሰራዊቱ የባህርዳርን እና አካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ እና የህገ-ወጥ ሀይሉን እኩይ ምኞት በማክሸፍ ታላቅ ስራ ተሰርቷል ብለዋል።

መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍና አቅርቦት ካደረገልን በህገ-ወጥ ሀይሉ የተነሳ በክልላችን የተፈጠውን የፀጥታ ችግር በመቀልበስ በሰላም እጦት የተቸገረውን ህዝባችንን ለማገልገል ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የከተማዋን ዘላቂ ሰላም ለማስጠበቅና ነዋሪዎቿን የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ በተሰሩ የወንጀል መከላከል፣የወንጀል ምርመራ ፣በትራፊክ ቁጥጥር ስራ እና የህግ ማስከበር ተግባር የተሻሉ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።

በስነልቦናና በሎጀስቲክ የዳበረ ሰራዊት የውጊያ ሚዛንን ይቀይራል የሚሉት ተሳታፊዎቹ የክልሉ ፖሊስ ተቋም ከክልሉ መንግስት ጋር በመሆን ለፖሊስ ሰራዊቱ ተገቢውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን እዉቅና ሰጥተዋል ፣ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ፍላጎታቸዉን ገልፀዋል ።

ዉይይቱ በሌሎች ቀጠናዎች ተጠናክረዉ እንደሚቀጥሉ ከመድረኩ ተገልጿል ።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top