“ሕዝቡ የምርጫው ባለቤት ሆኖ ለጸጥታ ሥራው አጋር እንዲሆን ጥሪ እናቀርባለን።” ምክትል ኮሚሽነር አበበ ውቤ
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬት በቂ ዝግጅት ማድረጉን አስታውቋል።
7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነጻ እና ፍትሐዊ በሆነ መልኩ እንዲጠናቀቅ በቂ ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን የአማራ ክልል ፖሊስ ገለጸ።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነርና የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር አበበ ውቤ እንደገለጹት፤ ሕዝቡ ያለምንም የጸጥታ ስጋት እንዲመርጥ ፖሊስ ትልቅ ኃላፊነትና አደራ አለበት። ይህንን አደራ ለመወጣትም ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ ያሉ የፖሊስ መዋቅሮች ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ፖሊስ ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ የገለጹት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ ዋና ዋናዎቹን ነጥቦች እንደሚከተለው ዘርዝረዋል፦
ለፖሊስ አባላት ስለ ምርጫ አስፈጻሚነትና ገለልተኝነት የግንዛቤ ፈጠራ መድረኮች ተዘጋጅተው ስልጠና ተሰጥቷል።
የምርጫ ቁሳቁሶች ካለምንም የጸጥታ ችግር ወደየቦታቸው እንዲንቀሳቀሱና ጥበቃ እንዲደረግላቸው እየተደረገ ይገኛል።
ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር ከዕቅድ ጀምሮ በጋራ እየተሰራ ሲሆን፣ ጠንካራ የወንጀል መከላከል ስራ እየተከናወነ ነው።
ፖሊስ በሕግ የሚፈቀድለትን የሙያ መመሪያና ሥርዓት መሠረት በማድረግ ተግባሩን በታማኝነትና በቁርጠኝነት እንደሚወጣ ተገልጿል።
ምክትል ኮሚሽነር አበበ ውቤ አክለውም፣ ሕዝቡ የምርጫው ባለቤት መሆኑን ተገንዝቦ ለጸጥታ ስራው አጋር እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።
እስካሁን ባለው ሂደት ምንም ዓይነት የጸጥታ ችግር አለማጋጠሙን የጠቀሱት ምክትል ኮሚሽነሩ በቀጣይም ሂደቱ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ እንዲጠናቀቅ ፖሊስ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ አስገንዝበዋል።

