የፖሊስ ተቋምን በማዘመን ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት ለመስጠት ደረጃውን የጠበቀ የሥራ አካባቢ መፍጠር የሪፎርሙ አንዱ ወሳኝ አካል መሆኑ ተገለጸ።

የፖሊስ ተቋምን በማዘመን ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት ለመስጠት ደረጃውን የጠበቀ የሥራ አካባቢ መፍጠር የሪፎርሙ አንዱ ወሳኝ አካል መሆኑ ተገለጸ።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ በተገኙበት ስትራቴጂክ እና ከፍተኛ አመራሮች በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ እየተገነባ የሚገኘውን ዘመናዊ የቢሮ ግንባታ ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ወቅት የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ በሪፎርሙ ልዩ ትኩረት ከተሰጡት መካከል ፣ ፖሊስ ራሱን በማዘመን ዲጅታላይዜሽን ስራዎችን በማላመድና ፣ውጤታማ ሥራ ለመከወን ምቹና የስራ ከባቢ ዘመኑን የዋጀና ቴክኖሎጂ የሚጠቀም የፖሊስ አገልግሎት መስጠት ይጠበቅበታል ብለዋል።

የክልሉ ፖሊስ ተቋም እያከናወነ ካለው የሪፎርም ሥራዎች መካከልም ዘመናዊ የቢሮ ግንባታዎችን በሁሉም ዞኖች ተደራሽ ማድረግ አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል።

የባህር ዳር ከተማ ፖሊስ መምሪያ የዋና ጠቅላይ መምሪያውን ፈለግ በመከተል ግንባታውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቅ መቻሉ የሚያኮራ ተግባር መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነሩ፣ ግንባታው በቅርቡ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ አሳስበዋል።

ኮሚሽነር ጀነራሉ ፣አክለውም በወንጀል መከላከል፣ በምርመራና በትራፊክ ቁጥጥር ተግባራት ላይ የፖሊስን እሴት በጠበቀ መልኩ ሕዝብን በታማኝነትና በቅንነት ማገልገል ቀዳሚ ኃላፊነት መሆኑን አሳስበዋል።

ዘመኑን የዋጀ የሥራ ቦታ ለውጤታማነት መሰረት ነው ያሉት ኮሚሽነር ጀነራሉ ለግንባታው መሳካት ድጋፍ ላደረጉት የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ እና ማኔጅመነ‍ታቸዉን ምስጋና አቅርበዋል።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው በበኩላቸው፣ የቢሮ ግንባታው አገልጋይና ተገልጋይን የሚያረካ አሠራርን ለማስፈን ከተወሰዱ ቁልፍ እርምጃዎች አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።

ግንባታውን በአጭር ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ወደ ሥራ በመግባት የከተማዋን ሰላም ማረጋገጥና ሕዝብን በብቃት ማገልገል ይኖርብናል ሲሉም ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው ገልጸዋል ።

የተጀመረው አዲስ ግንባታ የክልሉ ፖሊስ የጀመረውን የለውጥ ጉዞ የሚያጠናክርና ለወንጀል መከላከል ስምሪት ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑንም አመላክተዋል።

በከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ ስር የሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎችን ከማዘመንና ከማደስ አኳያም ስራዎች መጀመራቸውን ኮማንደር ዋለልኝ ጠቁመዋል።

የከተማዋን ሰላም በማስጠበቅና ህዝቡን የልማት ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ በትኩረት እየሰሩ እንደሚገኙም አረጋግጠዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top