የድል ዋንጫውን ተቋሙ በክብር ተረከበ

የድል ዋንጫውን ተቋሙ በክብር ተረከበ

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የመረብ ኳስ ጤና ቡድን በ2018 ዓ.ም የጤና ጨዋታዎች ያስመዘገበውን ድልና ያገኘውን የሻምፒዮናነት ዋንጫ ለተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች በክብር አስረከበ።

የድል ዋንጫውን የተረከቡት የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ቡድኑ ያስመዘገበው ውጤት ከስፖርታዊ ድል ባለፈ ተቋሙ ከህዝብ ጋር ያለውን ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር ትልቅ ሚና ተጫውቷል።

ኮሚሽነር ጀነራሉ ለቡድኑ አባላት ምስጋናቸውን በማቅረብ፣ በቀጣይ በደብረ ማርቆስ ከተማ ለሚከናወነው የአሸናፊዎች አሸናፊ የመረብ ኳስ የጤና ቡድኖች ውድድር ተቋሙ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

ቡድኑ ውጤታማነቱን በዘላቂነት እንዲያስቀጥልም በመዋቅር ተይዞ በቋሚነት መቀጠል እንደሚኖርበትም ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ጠቁመዋል።

ለተመዘገበው ውጤት ማበረታቻ ይሆን ዘንድም የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የገንዘብ ሽልማት አበርክቷል።

ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) አክለውም እንደ መረብ ኳስ ቡድኑ ሁሉ የእግር ኳስ ጤና ቡድኑም ስኬታማ እንዲሆን ተገቢው ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

የዋና ጠቅላይ መምሪያው የኮሙኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ በበኩላቸው፤ ይህ ውጤት ፖሊስ በፀጥታው ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በሁሉም መስኮች ውጤታማ መሆኑን የሚያሳይ ድል ነው ብለዋል።

ውጤቱ የፖሊስና የማህበረሰቡን ግንኙነት ለማጠናከር ያለውን ፋይዳም አጉልተዋል።

የቡድኑ መሪ ምክትል ኮማንደር አሰፋ ብርሃን በበኩላቸው፣ የተደረገላቸው አቀባበልና ድጋፍ ለቀጣይ ስራ ከፍተኛ መነቃቃትን የሚጥር መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይ ውድድሮችም የሻምፒዮናነት ክብራቸውን ለማስጠበቅ በትኩረት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

የቡድኑ አባላትም በተደረገላቸው ድንቅ አቀባበልና የገንዘብ ሽልማት የተሰማቸውን ከፍተኛ ደስታ በመግለጽ ለቀጣይ ውድድሮች ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top