“ምቹ የሥራ ቦታ ለተሻለ አገልግሎት አሰጣጥ ቁልፍ ሚና አለው” ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር)

“ምቹ የሥራ ቦታ ለተሻለ አገልግሎት አሰጣጥ ቁልፍ ሚና አለው” ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር)

የደሴ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ የ4ኛ ዋና ፖሊስ ጣቢያን ደረጃውን በጠበቀና በዘመናዊ መልክ ያስገነባውን ባለብዙ አገልግሎት ቢሮ በይፋ አስመረቀ።

በደመቀ ሁኔታ በተከናወነው በዚህ የምርቃት ሥነ-ሥርዓት ላይ ከፍተኛ የክልልና የዞን የሥራ ኃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በምርቃቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ተቋሙ የጀመረው የሪፎርም ጉዞ ዋና ዓላማ የፖሊስ አባላት በሥራ ቦታቸው ደስተኛ ሆነው ሕዝቡን በክብር ማገልገል የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነው ብለዋል።

ከቆርቆሮ ቢሮ ወጥተን እንዲህ ዓይነት ዘመናዊ ቢሮዎችን መገንባታችን የሪፎርማችንን ግብ በተግባር ያሳካ መሆኑን የሚያሳይ ነው ያሉት ኮሚሽነር ጀነራሉ ለዚህ ስኬት ጉልህ ድጋፍ ላደረጉት የክልሉ ፕሬዝዳንት፣ የደሴ ከተማ አስተዳደር፣ የደሴ ከተማ ባለሀብቶችና ማህበረሰቡ በአማራ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ስም ምስጋና አቅርበዋል።

የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር እሸቱ የሱፍ በበኩላቸው፤ ዘመናዊ ተቋምን መገንባት ሰላም የሰፈነባት ከተማን ለመፍጠር የማይተካ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

ይህ አዲስ ጣቢያ ተገልጋዮች ጉዳያቸውን በግልጽነት፣ በፍጥነትና ሰብዓዊ ክብራቸው ተጠብቆ እንዲስተናገዱ ሰፊ ዕድል እንደሚፈጥርም አመላክተዋል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ፤ ግንባታው ለከተማዋ ማህበረሰብ የሚሰጠው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፣ በቀጣይም ለመምሪያው ቢሮ ግንባታ የሚሆን ቦታ ለማስረከብ ቃል ገብተዋል።

ይህ ዘመናዊ ቢሮ በ56 ሚሊዮን ብር ወጪ በሁሴን ምሳዬ እና ጓደኞቻቸው የሕብረት ሽርክና ማህበር ሙሉ ድጋፍ የተገነባ ሲሆን በውስጡም 38 ልዩ ልዩ የቢሮ ክፍሎችን፣ 100 ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል መሰብሰቢያ አዳራሽ፣ የዳታ ማዕከል እና ልዩ የስነ-ልቦና ማማከሪያ ክፍልን ያካተተ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ለተገልጋዮችና ለሠራተኞች ምቾት ተብሎ ዘመናዊ ካፌ፣ የሻወርና የመጸዳጃ አገልግሎቶች እንዲሁም ለተቋሙ ጥበቃ በሚያግዙ የጥበቃ ማማዎች ተሟልቶ የተገነባ የሪፎርሙ ስኬት ማሳያ እንደሆነም ተጠቁሟል።

በመጨረሻም ለቢሮው ግንባታ መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ለነበራቸው አካላት የእውቅናና የምስጋና ሽልማት የተበረከተላቸው መሆኑን ከደሴ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ሕዝብ ግንኙነት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በተያያዘም የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር)፣ የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር እሸቱ የሱፍ፣እና ሌሎች የክልልና የዞን ከፍተኛ አመራሮች በደሴ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

በጉብኝታቸውም የባህርሸሽ አስፓልት መንገድ፣ የቧንቧ ውሃ ባሕል አምባ የኮሪደር ልማት እና የሕዝብ ኤሌክትሪክ ባስ አገልግሎትን የተመለከቱ ሲሆን በከተማዋ ያለው አስተማማኝ ሰላም ለነዚህ የልማት እንቅስቃሴዎችና ለገጽታ ግንባታ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አመራሮቹ ገልጸዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top