የደሴ ከተማ አስተዳደር ለፀጥታ አባላት የቤት መሥሪያ ቦታ አስረከበ
የደሴ ከተማ አስተዳደር የሀገርን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር በቁርጠኝነት ለሚሰሩ የፀጥታ መዋቅር አባላት እውቅና ለመስጠትና የኑሮ ጫናቸውን ለመቀነስ ቃል የገባውን መነሻ በማድረግ፣ በዛሬው ዕለት ለ2 ሺህ 900 የጸጥታ አባላት የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ርክክብ ፈጽሟል።
ርክክቡ የተከናወነው በደሴ ከተማ ቁርቁር ቀበሌ “ባህረ-ሰዮ” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሲሆን፣ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) ጨምሮ ከፍተኛ የክልልና የዞን የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) የክልሉ መንግስትና የደሴ ከተማ አስተዳደር ለጸጥታ ኃይሉ የሰጡትን እውቅና በማድነቅ፣ ይህ ተግባር አባላቱ በሙሉ ልብ ለሰላም እንዲሰሩ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
ሀገርን ለማጽናት የሚከፈለውን ዋጋ የሚያክል ባይሆንም መሰል ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ከተማ አስተዳደሩ የጸጥታ ሀይሉ ለክልሉ ሰላም መከበር እየከፈለ ያለውን የህይወት መስዋዕትነት በመረዳት ለፈጸመው ተግባር በክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ስም ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል
የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር እሸቱ የሱፍ በበኩላቸው፣ ሀገርን ለማጽናት እና ሰላም ለማስከበር ለሚሰሩ የፀጥታ አካላት የመኖሪያ ቤት እንዲኖራቸው መደረጉ የሚበረታታ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
የክልሉ መንግስትም የከተማ አስተዳደሩ የጀመረውን ይህን አበረታች ተግባር ዳር ለማድረስ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ እንደገለጹት ፤ መንግስት ከሚያከናውናቸው ሰው ተኮር ተግባራት መካከል የዜጎችን የመኖሪያ ቤት የማግኘት መብት ማረጋገጥ አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም ሀገርን በታማኝነት በመጠበቅ መስዋዕትነት እየከፈሉ ላሉ የፀጥታ አባላት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ክልሉ ባዘጋጀው መመሪያ ጋር በማጣጣም ለፀጥታ መዋቅሩ የቤት መሥሪያ ቦታ ለማዘጋጀት ሲሰራ መቆየቱን የገለጹት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው፣ በዛሬው ዕለትም በቁርቁር ቀበሌ “ባህረ-ሰዮ” በተባለ ቦታ በ125 ማህበራት ለተደራጁ ለ2 ሺህ 900 የፀጥታ አባላት የቦታ ርክክብ መካሄዱን አረጋግጠዋል።
በዚህም መሰረት በከተማዋ በማህበር ለተደራጁ የቤት ፈላጊዎች 117 ሄክታር መሬት በማዘጋጀት ለእያንዳንዱ አባል 100 ካሬ ሜትር ቦታ እንዲረከቡ መደረጉን ተናግረዋል።
አቶ ሳሙኤል አክለውም፣ በቦታው ላይ ግንባታ ከመጀመሩ በፊት አስፈላጊው መሠረተ ልማት እንደሚሟላላቸው ቃል ገብተዋል።
ለዓመታት ሲያቀርቡት የነበረው የቤት መስሪያ ቦታ ጥያቄ ምላሽ በማግኘቱ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው የገለጹት የፀጥታ አባላቱ፣ በተቀመጠው መስፈርትና መመሪያ መሰረት ግንባታውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመጀመር ዝግጁ መሆናቸውን በቁርጠኝነት ገልጸዋል።













