የአማራ ክልል ፖሊስ መረብ ኳስ የጤና ቡድን ተጋጣሚውን በመርታት የድል ባለቤት ሆነ።

የአማራ ክልል ፖሊስ መረብ ኳስ የጤና ቡድን ተጋጣሚውን በመርታት የድል ባለቤት ሆነ።

ለወራት በታላቅ ድምቀት ሲካሄድ የቆየው የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የመስሪያ ቤቶች የመረብ ኳስ የጤና ጨዋታ ዛሬ ፍፃሜውን ሲያገኝ፣ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የጤና ቡድን የዋንጫ ባለቤት በመሆን ታሪክ ሰርቷል።

በጉጉት ሲጠበቅ በነበረው የፍፃሜ ፍልሚያ የአማራ ክልል ፖሊስ ቡድን ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክ ኮሌጅ ጋር ተገናኝቶ ነበር።

ጨዋታው በሁለቱም ወገኖች በነበረው ብርቱ ፉክክርና የስፖርታዊ ጨዋነት መንፈስ የታጀበ ሲሆን በመጨረሻም ፖሊስ 3 ለ 1 በሆነ ሰፊ ውጤት በማሸነፍ የሻምፒዮንነቱን ዋንጫ ከፍ አድርጓል።

በዕለቱ ተገኝተው ጨዋታውን ከተመለከቱት ከፍተኛ አመራሮች መካከል የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የኮሙኒኬሽን እና ህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወንዴ የጤና ስፖርቱ በተቋማት መካከል ያለውን የስራ ቅንጅት ከማጠናከሩ ባለፈ ፖሊስ ከማህበረሰቡ ጋር ያለውን የጠበቀ ግንኙነት በማሳደግ በጋራ ወንጀልን ለመከላከል ትልቅ ድልድይ እየሆነ ይገኛል ብለዋል።

ፖሊስነትና አሸናፊነት የተቆራኙ መሆናቸውን በሜዳ ላይ ጭምር እያሳየ የሚገኘው የአማራ ክልል ፖሊስ ስፖርቱን ለጤና ብቻ ሳይሆን ለላቀ የሙያ ስኬትና ለተጠናከረ ህዝባዊ ትስስር እየተጠቀመበት እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

ይህ ድል ፖሊስ ከመደበኛ ተግባሩ ባሻገር ከማህበረሰቡ ጋር ያለንን ማህበራዊ ትስስርና ለጤና ያለውን ትኩረት ያረጋገጠበት ነው።

ስፖርት መልካም ግንኙነትን ለመገንባት ትልቅ አቅም ያለው መሳሪያ ነው ያሉት ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ በዚህ ውድድር ተቋማዊ ክብራችንን ከፍ ከማድረጋችን በላይ ከማህበረሰቡ ጋር ያለንን ዝምድና ያጠናከረ ሆኖ ታይቷል ብለዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መመሪያ የሰው ሀብት አስተዳደር እና ልማት ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር አብዮት ሽፈራው በበኩላቸው ፖሊስ ከወንጀል መከላከልና ሰላም ማስጠበቅ ስራው ጎን ለጎን፣ በስፖርት ዘርፍ እንዲህ በንቃት መሳተፉ ከማህበረሰቡ ጋር ያለውን መልካም ግንኙነት የሚያሳይ ድልድይ ነው ብለዋል።

ስፖርት ጤናማና ንቁ የሰው ሃይል ከመፍጠር ባለፈ ከምንጠብቀው ህዝብ ጋር በፍቅርና በስፖርታዊ ጨዋነት እንድንገናኝ ያደርገናል።

ቡድናችን ዘንድሮ የተመሰረተ አዲስ ቢሆንም በአጭር ጊዜ ታሪክ መስራት መቻሉ ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጋሻው እንዳለው ስፖርቱ ሰራተኞች ንቁ እንዲሆኑ የእርስ በእርስ ግንኙነታቸው እንዲዳብር እና በስራ ገበታቸው ላይ ውጤታማ እንዲሆኑ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው ብለዋል።

የ2018 ዓ.ም የጤና ጨዋታ አሸናፊ የሆነው የፖሊስ ቡድን በቀጣይ በግንቦት ወር በደብረ ማርቆስ ከተማ ለሚካሄደው የአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር ማለፉን አብስረዋል።

ቡድኑ ለዚህ ትልቅ መድረክ ጠንካራ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እንዲያከናውንም አሳስበዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የኮሙኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነት ዋና መምሪያ የስፖርት ዋና ክፍል ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር አንተነህ ጥሩአየሁ እንደገለጹት፤ የተቋሙ የመረብ ኳስ ጤና ቡድን በዛሬው ዕለት ያስመዘገበው ውጤት ለቀጣይ ውድድሮች ትልቅ ተስፋን የሰነቀና የተቋሙን መልካም ስም በደመቀ ሁኔታ ያስጠራ ሆኗል።

ኃላፊው አክለውም ተጫዋቾች በሜዳ ላይ ያሳዩት ስፖርታዊ ጨዋነት እና ያሳዩት ማራኪ እንቅስቃሴ የህዝብን ቀልብ መሳብ የቻለ ከመሆኑም በላይ የተቋሙን ክብርና ዝና ከፍ አድርጎ አሳይቷል ብለዋል።

ይህ የስፖርት መድረክ በመስሪያ ቤቶች መካከል ያለውን ወንድማማችነት፣ ትብብርና አጋርነት ይበልጥ በማጠናከር ረገድ የጎላ ሚና እንደሚጫወትም ገልጸዋል።

ቡድኑ በመረብ ኳሱ ካሳየው ድንቅ ብቃት በተጨማሪ በእግር ኳስ ውድድሮችም የተሻለ ጨዋታ በማድረግ የዋንጫ ባለቤት እንደሚሆንና የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ እየተዘጋጀ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የቡድኑ ኮከብ አሰልጣኝ የሆነው ዋና ሳጂን ጌቱ ካሚል ለውጤቱ መገኘት የተቋሙ ድጋፍና የተጫዋቾች ጥረት ከፍተኛ መሆኑን ገልጾ፣ ወደፊትም በስፖርት አማካኝነት ፖሊስንና ህዝብን ይበልጥ ለማቀራረብ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጧል።

ቀጣይ ግንቦት ላይ ለሚደረገው የመስሪያ ቤቶች የአሸናፊዎች አሸናፊ የጤና መረብ ኳስ ውድድር ዝግጅታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ጠቁመዋል።

ቡድኑ ከዋንጫው በተጨማሪም የጨዋታው ኮከብ ተጫዋች ዋና ሳጅን ሙሉአለም ተክሉ እና ኮከብ አሰልጣኝ ዋና ሳጅን ጌቱ ካሚል በመሆንም ሽልማቶችን በመጠቅለል ደማቅ ድርብ ድል አስመዝግቧል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top