“የሕዝባችንን ሰላም የሚያውኩ ህገ-ወጥ አካላትን በአጭር ጊዜ ውስጥ በማጽዳት የክልሉን ሕዝብ የሰላምና የልማት ተጠቃሚ ማድረግ ለነገ የማይባል የትኩረት ሥራችን ነው”! ምክትል ኮሚሽነር አበበ ውቤ።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ከፍተኛ አመራሮች በሰሜን ጎጃም ዞን በሚገኘው የግንባር ቀጠና በመገኘት የሰራዊቱን የግዳጅ አፈጻጸም ገመገሙ።
ከፍተኛ አመራሮቹ ከ40ኛ እና 12ኛ ሻለቃ የአድማ መከላከል ፖሊስ አባላት ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ በክልሉ ሰላም ማስከበር ስራና ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታዎች ዙሪያ ሰፊ ውይይት አድርገዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነርና የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር አበበ ውቤ፤ ማንኛውንም የተሰጠ ግዳጅ በብቃትና በውጤታማነት ለመቋጨት ዋነኛው መሠረት የዓላማ ፅናት፣ የተቋም እና የሙያ ፍቅርን መላበስ መሆኑን ገልጸዋል።
እስካሁን ከተገኙ ድሎች ተሞክሮ በመውሰድ የሕዝባችንን ሰላም በዘላቂነት ማረጋገጥ እንደሚገባም አሳስበዋል።
የአገር አፍራሽ ህገ-ወጥ ኃይሎችና የውጭ ባዳዎችን እኩይ ሴራ ለማክሸፍ በርካታ መስዋዕትነት መከፈሉን ያስታወሱት ምክትል ኮሚሽነር አበበ ትግሉ ፍሬ አፍርቶ ከታቀደው ግብ እንዲደርስ ህገ-ወጥና ተላላኪ ኃይሎችን አንገት የሚያስደፋ ተጋድሎ ማድረግ የግድ እንደሚል አስገንዝበዋል።
እንደ ምክትል ኮሚሽነር አበበ ውቤ ገለጻ “የሕዝባችንን ሰላም የሚያውኩ ህገ-ወጥ አካላትን በአጭር ጊዜ ውስጥ በማጽዳት የክልሉን ሕዝብ የሰላምና የልማት ተጠቃሚ ማድረግ ለነገ የማይባል የትኩረት ሥራችን ነው” ሲሉም አመላክተዋል።
ምክትል ኮሚሽነሩ አክለውም 7ኛውን ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ ህገ-ወጥ አካላትን ሴራ በማክሸፍ፤ ምርጫው ሰላማዊ፣ የተረጋጋና ፍትሐዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በልዩ ትኩረት መሥራት እንደሚገባ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር እና የአስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ረዳት ኮሚሽነር አያልነህ ተስፋዬ በበኩላቸው የአድማ መከላከል ፖሊስ አባላት የገጠሟቸውን ፈተናዎች በጽናት ተቋቁመው ድልን እያስመዘገቡ መሆኑን ገልጸዋል።
በብዙ መከራዎች ውስጥ አልፋችሁ፣ በጨለማ ውስጥ እንደ ሻማ በርታችሁ የሕዝባችሁን ሰላም ለማረጋገጥ የምትተጉ ባለታሪኮች ናችሁ ሲሉም ለሰራዊቱ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።
ፖሊስ ከሀገር መከላከያ ሰራዊትና ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ሀገርን ከመፍረስና ሕዝብን ከመበተን ለመታደግ እያከናወነ ያለው ተግባር የሚደነቅ መሆኑን ጠቁመው፣ በቀጣይም በሰላም እጦት የተጎሳቆለውን ሕዝብ ነፃ ለማውጣት በትጋት መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የክልሉ ፖሊስ በሰው ኃይል ግንባታ፣ በምርመራና በወንጀል መከላከል ዘርፍ ያከናወናቸው የሪፎርም ሥራዎች ውጤት እያመጡ መሆኑን የጠቆሙት ረዳት ኮሚሽነር አያልነህ በተለይም የአድማ መከላከል ፖሊስን በሰው ኃይልና በሎጅስቲክስ የማጠናከሩ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የአድማ መከላከል ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር አወቀ ሞትባይኖር ፣ የሰራዊቱ ትልቁ መሣሪያ የወኔና የስነ-ልቦና ዝግጁነት መሆኑን ጠቁመዋል።
ረዳት ኮሚሽነር አወቀ አክለውም አባላቱ ለገቡት ቃለ-መሐላና ለመለዮ ክብራቸው ታማኝ ሆነው እንዲቀጥሉ መክረዋል።
በግዳጅ ቀጠናው የሚገኙ የ40ኛ እና 12ኛ ሻለቃ አመራሮችና አባላት በበኩላቸው፣ ከፍተኛ አመራሮቹ ምሽግ ድረስ መጥተው ጉብኝትና ውይይት ማድረጋቸው ሞራላቸውን እንዳሳደገው ገልጸዋል።
ለሕዝባችን ሰላምና ለሀገር መረጋጋት ሲባል ህይወታችንን ሳንሰስት በመስጠት የሕዝብን ሰላም የሚያውኩ አካላትን በማጽዳት የሕዝባችንን ሰላም እናረጋግጣለን ሲሉ ቁርጠኝነታቸውን አረጋግጠዋል።
አመራሮቹ የሕግ ማስከበር ዘመቻው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና የሕዝብን ሰላም ለማረጋገጥ የሚከፈለው መስዋዕትነት ታሪካዊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ይህ የግምገማና የውይይት መድረክ በሌሎች የአድማ መከላከል ሻለቆችም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል።











