በደብረ ብርሃን ከተማ ህገ-ወጥ የኮንትሮባንድ ክምችት በቁጥጥር ስር ዋለ
በደብረ ብርሃን ከተማ እቴጌ ጣይቱ ክፍለ ከተማ፣ ጊዮርጊስ ቀበሌ ልዩ ቦታው ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ዝቅ ብሎ በሚገኝ አካባቢ፤ ከአንኮበር ተጭኖ የመጣ ከፍተኛ መጠን ያለው የኮንትሮባንድ እቃ በቁጥጥር ስር መዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።
የታርጋ ቁጥሩ B73479 አ/አ የሆነ የጭነት አይሱዙ መኪና፣ ከአንኮበር ወደ ደብረ ብርሃን ከተማ ህገ-ወጥ የኮንትሮባንድ እቃዎችን ጭኖ በመግባት በምሽት 1:00 ሰዓት አካባቢ መጋዘን ውስጥ ሲያራግፍ በደረሰ ጥቆማ መሠረት ክትትል ሲደረግበት ቆይቷል።
ፖሊስ እቃው በሚራገፍበት ቦታ ላይ በደረሰበት ወቅት፣ ማንነታቸው ያልታወቁ ግለሰቦች መኪናውንና መጋዘኑን እንደተከፈቱ ትተው በመሰወራቸው በቁጥጥር ስር ለማዋል ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
በአካባቢው ሰላም ወዳድ ማህበረሰብና ወጣቶች ትብብር ከመጋዘኑ ውስጥ ተጭነው ወደ ፖሊስ ጣቢያ የገቡት የኮንትሮባንድ እቃዎች ሻምላ ሲጋራ፤ የሺሻ ሙዓሰል እና ሌሎች እስካሁን ዝርዝራቸው ያልተለየ በርካታ የኮንትሮባንድ ቁሳቁሶች መሆናቸውን ፖሊስ አስታውቋል።
እነዚህ ቁሳቁሶች ብዛት በመሆናቸው 3 ሲኖ ትራክ እና 1 አይሱዙ መኪናዎችን ሙሉ የጫኑ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት መጠናቸውና የገንዘብ ግምታቸው እየተጠና መሆኑ ተገልጿል።
ህገ-ወጥ እቃው ተከዝኖበት የነበረው ቤት አከራይ አቶ ደበበ ሰይፈ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው ይገኛል።
ጋቢናው ተቆልፎ ሾፌሩ የተሰወረበት አይሱዙ መኪናም በቦታው ጥበቃ እየተደረገለት ያደረ ሲሆን፣ በውስጡ የነበረው እቃ ግን ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንዲጓጓዝ ተደርጓል።
ፖሊስ ባስተላለፈው መልዕክት ‘ከህዝብ የሚደበቅ ህገ-ወጥነት የለም’ በማለት የዜጎችን ጤና እና ምርታማነት የሚጎዱ የሱስ ምንጮችን ለማድረቅ ህብረተሰቡ እያደረገ ያለው ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል።
በተጨማሪም እንዲህ ያሉ ህገ-ወጥ ተግባራትን በቁጥጥር ስር ለማዋል በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ በቁርጠኝነትና በተግባር የመስራት አስፈላጊነት ላይ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ፖሊስ አሳስቧል።







