በአሰቃቂ ሁኔታ ሰው በመግደል ወንጀል የተከሰሱት ሁለት ግለሰቦች በጽኑ እስራት ተቀጡ

በአሰቃቂ ሁኔታ ሰው በመግደል ወንጀል የተከሰሱት ሁለት ግለሰቦች በጽኑ እስራት ተቀጡ

በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዳንግላ እና በእንጅባራ ከተሞች የሰው መግደል ወንጀል በፈጸሙ ሁለት ተከሳሾች ላይ ከባድ የጽኑ እስራት ውሳኔ ማሳለፉን አስታወቀ።

በእንጅባራ ከተማ 02 ቀበሌ ውዴ አስሪት በሚባል አረቄ ቤት ውስጥ ተከሳሽ በጎሰው አወቀ በታጣፊ ክላሽንኮቭ መሣሪያ በመጠቀም የሁለት ሰዎችን ህይወት አጥፍቷል።

ተከሳሹ አድነው ጌታሁንን ግንባሩን እንዲሁም ሀብታም አምሳሉን ደረቷን በጥይት በመምታት ህይወታቸው እንዲያልፍ አድርጓል።

ጉዳዩን ሲመረምር የቆየው የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተከሳሹ የፈጸመው ወንጀል በሰውና በሰነድ በማረጋገጡ ሚያዚያ 16 ቀን 2018 ዓ.ም በዋለው መደበኛ ችሎት በፈጸመው ተደራራቢ የግድያ ወንጀል በ25 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ አስተላልፏል።

በተመሳሳይ በዳንግላ ከተማ ዘለሳ ሲማልታ ቀበሌ ወረቡ ሽሃ በተባለ ስፍራ መምህር ሲሳይ ሙሉቀን ላይ አሰቃቂ ግድያ የፈጸመው ተከሳሽ ሽፈራው ይደረሳል አግደው በጽኑ እስራት ተቀጥቷል።

ተከሳሹ በዱላ ላይ በገጠመው ፈራድ በተባለ ስለታማ መሣሪያ በመጠቀም በፈጸመው አሰቃቂ ድብደባ ህይወታቸው እንዲያልፍ አድርጓል።

ፍርድ ቤቱም ተከሳሹ በፈጸመው ጭካኔ የተሞላበት ወንጀል ከፖሊስ የቀረበለትን የምርመራ መዝገብ በማረጋገጥና ሌሎች የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን በማገናዘብ ጥፋተኛ መሆኑን በማረጋገጥ ሚያዚያ 16 ቀን 2018 ዓ.ም በዋለው መደበኛ ችሎት ለሌሎች መሰል ድርጊት ፈጻሚዎች ማስተማሪያ ይሆን ዘንድ በ19 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top