ሙስና የሀገርን ኢኮኖሚ የሚያደቅ፣ የዜጎችን ተስፋ የሚያቀጭጭ፣ የዘመናችን የልማት እንቅፋት መሆኑ ተገለጸ

ሙስና የሀገርን ኢኮኖሚ የሚያደቅ፣ የዜጎችን ተስፋ የሚያቀጭጭ፣ የዘመናችን የልማት እንቅፋት መሆኑ ተገለጸ

የሙስና ወንጀል የህግ የበላይነትን በመሸርሸር፣ የመልካም አስተዳደር እጦትን በመፍጠር እና የሀገርን የሞራል ከፍታ በመናድ ለዘላቂ እድገት የሚደረገውን ጉዞ በብርቱ እያደናቀፈ ይገኛል።

ይህንን ስውር እና ረቂቅ ወንጀል ለመግታት በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የሙስና ወንጀሎች ምርመራ ዋና መምሪያ እያከናወነ ያለው ተግባር ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን እያመዘገበ ይገኛል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነርና የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው ሙስና በአንድ ሀገር ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መዋቅር ላይ የሚሰነዘር አደገኛ መርዝ በመሆኑ ይህንን ስጋት በመረዳት ወንጀሉን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ፖሊስ በልዩ ትኩረትና በተደራጀ መልኩ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

እንደ ምክትል ኮሚሽነሩ ገለጻ ለልማት ለትምህርትና ለጤና መዋል የነበረበት የህዝብ ሀብት በጥቂት ግለሰቦች ኪስ ውስጥ እንዲገባ በማድረግ የሀገርን እድገት ወደ ኋላ ይጎትታል።

ወንጀሉ ከተፈጸመ በኋላ ከመከታተል ባለፈ ወንጀሉ ሊፈጸምባቸው የሚችሉ ክፍተቶችን በማጥናትና የመከላከያ እርምጃዎችን በመውሰድ የሀገር ሀብት እንዳይባክን እያደረገ ነው ሲሉም አክለዋል።

ሙስናን መዋጋት ማለት የነገዋን ሀገርና የትውልዱን መፃኢ እድል መጠበቅ በመሆኑ እያንዳንዱ የመንግስት ተቋም አሰራሩን ለህዝብ ግልጽ ማድረግና የተጠያቂነት ስርዓት ማስፈን አለበት።

የክልላችን ፖሊስ እያከናወነ ያለው የተደራጀ የፀረ-ሙስና ትግል የሚበረታታ ቢሆንም፣ እያንዳንዱ ዜጋ ይህንን አውዳሚ ወንጀል በመታገል ረገድ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የሙስና ወንጀሎች ምርመራ ዋና መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ዳምጤ ባዬ ባለፋት ዘጠኝ ወራት በክልል ደረጃ በተፈፀመ የሙስና ወንጀል ከ1 ሺህ በላይ ጥቆማዎች ደርሰው ከ8 መቶ በላይ የሚሆኑ መዝገቦችን ምርመራ አጣርቶ ለአቃቤ ህግ መላኩን ገልጸዋል።

እንደ ኮማንደር ዳምጤ ገለፃ ከወንጀሉ ጋር በተያያዘም ከ93 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው በገንዘብና ከቀላል እስከ 16 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ተፈርዶባቸዋል ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ ከተመዘገቡ የሙስና ወንጀሎች ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው ህገወጥ የመሬት ወረራ እና የመንግስት ንብረት ምዝበራ ነው ያሉት ኃላፊው በበጀት ዓመቱም በህገወጥ መንገድ ከተወረረ ከ 1መቶ 40 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ መሬት ውስጥ ከ12ሺህ 5 መቶ በላይ ካሬ ሜትር መሬት ማስመለስ መቻሉንም አንስተዋል።

መመሪያን ሳያሟሉ በህገወጥ መንገድ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ሊረከቡ የነበሩ ከ2 መቶ 90 በላይ ማህበራት ላይ ምርመራ በማጣራት ለአቃቢ ህግ መላኩን የጠቆሙት ኮማንደር ዳምጤ በዚህም ከ1ሚሊዮን በላይ ካሬ ሜትር መሬትን ማስቀረት ተችሏል ብለዋል።

ከህገወጥ የመሬት ወረራ በተጨማሪም በሀሰት የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከመንግስት የተመዘበረን ከ80ሚሊዮን 7መቶ ሺህ ብር በላይ ምርመራ በማጣራት በፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዲታገድ ተደርጓል ብለዋል።

ሙስና የሀገርን ኢኮኖሚ የሚያደቅ፣ የዜጎችን ተስፋ የሚያቀጭጭ፣ የዘመናችን የልማት እንቅፋት መሆኑ የጠቆሙት ኃላፊው የህግ የበላይነትን በመሸርሸር፣ የመልካም አስተዳደር እጦትን በመፍጠር እና የሀገርን የሞራል ከፍታ በመናድ ለዘላቂ እድገት የሚደረገውን ጉዞ በብርቱ እያደናቀፈ ይገኛል ብለዋል።

የሙስና ወንጀል ከሌሎች የወንጀል ድርጊቶች በበለጠ መልኩ በረቀቀ እና በስውር የሚፈፀም በመሆኑ የምርመራ ስራውን ፈታኝ እንዳደረገውም ኮማንደር ዳምጤ ባዬ አረጋግጠዋል ።

ቀደም ሲል ከስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ጋር ይከናወን የነበረው የምርመራ ስራ፣ አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ በክልሉ ፖሊስ ተረክቦ ከክልል እስከ ወረዳ ድረስ በተዘረጋ መዋቅር በአመርቂ ሁኔታ እየተከናወነ ይገኛል። ለዚህም የምርመራ ባለሙያዎች በየጊዜው የአቅም ግንባታና የስነ-ምግባር ስልጠና እንዲያገኙ እየተደረገ ነው።

ለወንጀሉ መባባስ የክልሉ የፀጥታ ሁኔታ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን የጠቆሙት ኮማንደር ዳምጤ ችግሩን ለመከላከል ሁሉም አካል በይመለከተኛል ስሜት ጥቆማ በመስጠትና ማስረጃ በመሆን የዜግነት ድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም አመላክተዋል።

የሀገር እድገት ጸርና የህብረተሰብን ሰላም የሚያናጋውን የሙስና ወንጀል የመከላከል ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ኃላፊው ጠቁመዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top