በባህር ዳር ከተማ አሰቃቂ ወንጀል ፈጽሞ ተሰዉሮ የነበረዉ በተደረገ ሰፊ ክትትል መቀሌ ከተማ መኖሩ ተረጋግጦ በቁጥጥር ስር የዋለው ተጠርጣሪ በዛሬው ዕለት በባህር ዳር ወንጀሉን በፈፀመበት ከተማ የከተማዉ ፖሊስ ተረክቧል።
በአንዲት ወጣት ላይ እጅግ አሰቃቂ የአስገድዶ መድፈርና የግድያ ወንጀል ፈጽሞ ሲፈለግ የነበረው ተጠርጣሪ ያምራል አለበል አለሙ፣ በፖሊስ ብርቱ ክትትል ዉስጥ እንደነበር መግለፃችን ይታወቃል ።
ተጠርጣሪው ወንጀሉን ከፈጸመ በኋላ ወደ ትግራይ ክልል በማምራት በመቐለ ከተማ ለመደበቅ ቢሞክርም፣ የአማራ ክልል ፖሊስ ባዋቀረው ልዩ የክትትልና የኦፕሬሽን ቡድን ሌት ተቀን ሲደረግ በቆየው ክትትል አማካኝነት ትናንት ሚያዚያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም በመቐለ ከተማ በቁጥጥር ስር መዋሉን አሳውቀን ነበር።
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ምክትል መምሪያ አዛዥ ኮማንደር መኳንንት አድማስ እንደገለጹት የፖሊስ ተቋም የሕዝብ ደህንነትን ለመጠበቅ የቆመ መሆኑን በማስታወስ፣ የተጠርጣሪው አስነዋሪ ድርጊት የፖሊስን ተቋም በፍጹም እንደማይወክል በፅኑ አሳስበዋል።
ድርጊቱ መላውን የክልሉን ሕዝብና የፖሊስ ሰራዊቱን በእጅጉ ያሳዘነ መሆኑንም አመላክተዋል።
በአሁኑ ወቅት በምርመራ ክፍሉ ምርመራው እየተጣራ እንደሚገኝና የምርመራ ሂደቱ ተጠናቆ የፍርድ ውሳኔ ሲያገኝ ውጤቱ ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግ ኮማንደር መኳንንት አድማስ አስታውቀዋል።
በየትኛውም ቦታም ሆነ ሁኔታ ወንጀል ፈጽሞ ማምለጥ እንደማይቻልም ኮማንደር መኳንንት አድማስ አረጋግጠዋል።




