በነፍስ ግድያ ወንጀል ተጠርጥሮ የነበረው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ
በሰው ሕይወት ማጥፋት ወንጀል ተጠርጥሮ ለተወሰነ ጊዜ ተሰውሮ የነበረው ግለሰብ በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ በቁጥጥር ስር መዋሉን የአማራ ክልል ፖሊስ አስታወቀ።
የአማራ ክልል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት፤ ያምራል አለበል አለሙ የተባለው ተጠርጣሪ ግድያ ፈጽሞ ከአካባቢው በመሰወር ሲፈለግ ቆይቷል።
ተጠርጣሪው ወንጀሉን ፈጽሞ ከተሰወረበት ጊዜ ጀምሮ ፖሊስ ጥብቅ ክትትል ሲያደርግ መቆየቱን ምክትል ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
በመጨረሻም በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ተሸሽጎ እንደሚገኝ በመረጋገጡ በተደረገ የተቀናጀ ስራ በቁጥጥር ስር ሊውል ችሏል።
ለዚህ ስኬታማ ስራ የትግራይ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ላበረከተው የላቀ አስተዋጽኦ ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ስም ምስጋና አቅርበዋል።
‘ወንጀል ፈጽሞ ለጊዜው ቢሰወርም ከሕግ ቁጥጥር ማምለጥ አይቻልም’ ያሉት ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ፤ ፖሊስ ወንጀልን የመከላከልና ተጠርጣሪዎችን ለሕግ የማቅረብ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የወንጀል ተጠርጣሪዎችን በማጋለጥና ለሕግ አሳልፎ በመስጠት ረገድ እየተደረገ ያለው ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እና በክልሎች መካከል ያለውን የጸጥታ ትብብር በማጠናከር የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በትጋት እንደሚሰራም ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው አጽንኦት ሰጥተው አብራርተዋል።


