ለአማራ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አሽከርካሪዎች የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ስልጠና ተሰጠ
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ከክልሉ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ጋር በመተባበር ለተቋሙ አሽከርካሪዎች የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ስልጠና ሰጠ።
ስልጠናው የአሽከርካሪዎችን ሙያዊ ብቃት ከማሳደግ ባለፈ፣ የተሽከርካሪ አያያዝ፣ የሥራ ላይ ስነ-ምግባር እና የተቋማዊ ኃላፊነት ስሜትን ለማጎልበት ያለመ ነው።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የሰው ሀብት አስተዳደር ልማት ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር አቢዎት ሽፈራው በስልጠናው መክፈቻ ላይ እንደገለጹት፣ አሽከርካሪነት ከፍተኛ ኃላፊነት የሚጠይቅ ሙያ ነው ብለዋል።
አሽከርካሪዎች ከሙያው ዕውቀትና ችሎታ ጎን ለጎን፣ መልካም የሥራ ስነ-ምግባርን መላበስና ሙያዊ ብቃታቸውን ማሳደግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
በሀገራችን የትራፊክ አደጋ የብዙዎችን ህይወት በመቅጠፍና ንብረት በማውደም ላይ እንደሚገኝ ያነሱት ረዳት ኮሚሽነሩ፣ አደጋው አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አስገንዝበዋል።
ለአደጋው መከሰት ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል የአሽከርካሪዎች ግንዛቤ ማነስ አንዱ መሆኑን በማስታወስ፣ አሽከርካሪዎች የሙያ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ በመወጣት አደጋውን በመከላከል ረገድ ግንባር ቀደም ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።
ከስልጠናውም ዘመናዊ የተሽከርካሪ አያያዝና አጠቃቀም ክህሎትን ማዳበር፣የተቋሙን ስም የሚመጥንና የተረጋጋ ሙያዊ ስነ-ምግባርን መገንባት፣የትራፊክ ህግጋትን በማክበር የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ የሚያስችል ግንዛቤ እንደሚቀስሙ ይጠበቃል።
በቀጣይም ተመሳሳይ የብቃት ማሻሻያ የስልጠና መድረኮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተመላክቷል።
ስልጠናው በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ እና በክልሉ መንገድ ትራንስፖርት ቢሮ በጋራ የተዘጋጀ እንደሆነም ተጠቁሟል።





