በአማራ ክልል የትራፊክ ደህንነትን ለማረጋገጥና ህገ-ወጥ የነዳጅ ዝውውርን ለመግታት የተከናወነው የተቀናጀ ቁጥጥር ውጤት እያመጣ መሆኑ ተገለጸ

በአማራ ክልል የትራፊክ ደህንነትን ለማረጋገጥና ህገ-ወጥ የነዳጅ ዝውውርን ለመግታት የተከናወነው የተቀናጀ ቁጥጥር ውጤት እያመጣ መሆኑ ተገለጸ

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ከአማራ ክልል መንገድ ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ቢሮ ጋር በመተባበር በሁሉም የክልሉ 22 ዞኖች ሲከናወን የቆየውን ሰፊ ህገ-ወጥ የነዳጅ ዝውውር፣ የትራፊክ ቁጥጥርና የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄን ገመገመ።

በግምገማ መድረኩ ላይ እንደተመላከተው፤ በጸጥታ ኃይሉ፣ በትራንስፖርትና በንግድ ቢሮ እንዲሁም በወጣት ማህበራት መካከል የተፈጠረው የተቀናጀ አሰራር በክልሉ ይታዩ የነበሩ ህገ-ወጥ ተግባራትን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ አስችሏል።

የአማራ ክልል መንገድ ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ጋሻው አወቀ እንደገለጹት የነዳጅ እጥረቱን ለመቅረፍና የዋጋ ግሽበቱን ለመከላከል ከፖሊስ ጋር በጋራ እቅድ በማውጣት፣ በሁሉም ዞኖች በቂ የሰው ኃይል ስምሪት አድርገን በመንቀሳቀሳችን ህገ-ወጥነትን በመቆጣጠር ረገድ ተጨባጭ ውጤት አግኝተናል ብለዋል።

ያለመንጃ ፈቃድ ማሽከርከር፣ የዓመታዊ ቴክኒክ ምርመራ (ቦሎ) የሌላቸውን ተሽከርካሪዎች መቆጣጠርና ከታሪፍ በላይ የሚያስከፍሉ አሽከርካሪዎች ላይ የተወሰደው እርምጃ አስተማሪና ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቱንም ገልጸዋል።

ለግዳጅ የተዘጋጀ ነው በሚል ሰበብ ነዳጅ አስቀድተው የሚሸጡ፣ ከማደያ ሰራተኞች ጋር በመመሳጠር በጥቁር ገበያ የሚያሻሽጡ ደላሎችና ነዳጅን ለህገ-ወጥ ንግድ የሚያውሉ ግለሰቦች ላይ ጥብቅ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል።

ከዚህም ባለፈ ባልተገባ መንገድ ማንነታቸው የማይታወቁ ቪ አይ ፒ ነኝ በማለት ወይም በጉቦ ነዳጅ ለማግኘት የሚሞክሩ አካላትን አሰራር በመስበር ረገድ የጸጥታ ኃይሉ የወሰደው ቁርጠኛ እርምጃ የሚደነቅ መሆኑንም ጠቁመዋል ።

ከቁጥጥሩ ጎን ለጎን ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች የተከናወኑ ሲሆን፤ ከመንገድ ትራንስፖርትና ንግድ ባለሙያዎች፣ ከትራፊክ ባለሙያዎች፣ ከነዳጅ ማደያ ሰራተኞች፣ ከወጣቶችና ከአሽከርካሪዎች ጋር ተከታታይ ውይይቶች መደረጋቸው የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ ረገድ ትልቅ ለውጥ መምጣቱን ገልጸዋል።

የክልሉ ፖሊስና የትራንስፖርት ቢሮ በቀጣይም ይህንኑ የተቀናጀ ስራ አጠናክረው በመቀጠል፣ በክልሉ አስተማማኝ የትራፊክ ደህንነትና ፍትሐዊ የነዳጅ ስርጭት እንዲሰፍን በትኩረት እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የትራፊክ ቁጥጥርና ደህንነት ዋና መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር በቀለ አብዬ በበኩላቸው ህገ-ወጥ የነዳጅ ዝውውርንና የትራንስፖርት እንቅስቃሴን ለመግታት የተወሰደው እርምጃ ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል።

ይሁን እንጂ አሁንም በፖሊስ፣ በትራንስፖርት ስምሪትና በንግድ ባለሙያዎች መካከል ሙያቸውን በታማኝነት ከሚወጡት ጎን ለጎን፣

ኃላፊነታቸውን ተገን በማድረግ የህዝብና የመንግስትን ንብረት የሚበዘብዙ ጥቂት የጸጥታ፣ የትራንስፖርትና የንግድ ባለሙያዎች ላይ እርምጃ መወሰዱንና በቀጣይም ክትትሉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

እንደ ኮማንደር በቀለ ገለጻ በነዳጅ ስርጭቱ ላይ የጸጥታ አካላት የተሰጣቸውን ሀላፊነት ለህገ-ወጥ ተግባር እየተጠቀሙ ነው የሚለውን የህዝብ ጥቆማዎች መሰረት በማድረግ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከመከላከያና ከሚሊሻ አመራሮች ጋር ግልጽ ውይይት መደረጉና ህገ-ወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተው በተገኙ የጸጥታ አካላት ላይ እርምጃ መወሰዱ ለስራው ስኬታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል ።

በህዝብ ላይ ጫና የሚፈጥሩ ግለሰቦችና ደላሎች ላይ የሚደረገው ቁጥጥር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና አጥፊዎችም ተገቢውን የህግ ቅጣት እንዲያገኙ እንደሚደረግ ኮማንደር በቀለ አብዬ ጠቁመዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች እንደገለጹት፣ በአሁኑ ወቅት በክልሉ የሚታየው የነዳጅ እጥረት ዋነኛው ምክንያት የምርት ማነስ ሳይሆን የቁጥጥር መላላት፣ በተቋማት መካከል የተቀናጀ አሰራር አለመኖርና በኩፖን አሰጣጥ ሂደት ላይ የሚታዩ የአሰራር ግድፈቶች መሆናቸውን አንስተዋል።

በትራንስፖርት አገልግሎት ረገድም አሽከርካሪዎች ከመነሃሪያ ውጪ ተሳፋሪዎችን ለተጨማሪ ክፍያ የሚዳርጉበት አሰራር ጥብቅ ክትትል ተደርጎ መቆም እንደሚኖርበትና ተግባሩን በሚፈጽሙ አሽከርካሪዎች ላይ የማያዳግም እርምጃ መወሰድ እንደሚኖርበትም ጠቁመዋል።

ተሳፋሪዎችም ችግሩ ሲፈጠር መድረሻ ላይ ደርሶ ቅሬታ ከማቅረብ ይልቅ፣ በወቅቱ ጥቆማ በመስጠት የአጥፊዎችን ተግባር እንዲያጋልጡ ተሳታፊዎች ጥሪ አቅርበዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም የችግሩን ምንጭ የሚያጠና ቡድን ወደ ስራ የገባ ሲሆን፣ የህዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎችን በግልጽ የመለየትና የመመዝገብ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ስምምነት ላይ ተደርሷል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top