በኢትዮጵያ የፖሊስ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ‘የወንጀል መከላከል አዛዦች ፎረም’ ተመሰረተ

በኢትዮጵያ የፖሊስ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ‘የወንጀል መከላከል አዛዦች ፎረም’ ተመሰረተ

በሀገራችን የፖሊስ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ተቋማዊ ትስስር ተጀመረ። የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ የሁሉም ክልል ፖሊስ ተቋማት እና የሁለቱ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ተቋማት የወንጀል መከላከል አዛዦችን የሚያቀናጅ ሀገራዊ ፎረም ለመጀመሪያ ጊዜ ተመስርቶ ስራውን ጀምሯል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ ፎረሙን በከፈቱበት ወቅት እንደገለጹት፣ የዚህ መድረክ መቋቋም ዋና ዓላማ በሁሉም የፖሊስ መዋቅሮች መካከል ጠንካራ የኦፕሬሽን ትስስር መፍጠር፣ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እና ሀገራዊ ፖሊሳዊ አንድነትን በመገንባት የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት በዘላቂነት ማረጋገጥ ነው ብለዋል።

የፖሊስ ተልዕኮአችን አንድ በመሆኑ፣ በቅንጅት በመሥራት የሀገራችንን ሰላም አስተማማኝ ማድረግ ይኖርብናል ሲሉ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ አክለዋል።

ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሉ በንግግራቸው ወቅት መጪው 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ፍጹም ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የፖሊስ የኦፕሬሽን ክፍል ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለበት አሳስበዋል።

የምርጫ ቁሳቁሶችን በሰላም ለሁሉም ጣቢያዎች ማድረስ፣ በየጣቢያዎቹ ጥብቅ ጥበቃ በማድረግ የዜጎችን የመምረጥ መብት ማስከበር፣ መንግስት ያስቀመጠውን የጸጥታ አቅጣጫ በጥራት ወደ ተግባር መቀየር እንደሚገባ ገልጸዋል።

የፖሊስ ስራ ድንበር የሌለውና ዓለም አቀፋዊ ባህሪ ያለው መሆኑን የጠቀሱት አዛዡ፣ በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩ የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት ፖሊስ ከሌሎች የጸጥታና ደኅንነት አካላት ጋር ተቀናጅቶ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

ይህም በሀገሪቱ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ያለምንም ስጋት እንዲቀጥሉና ዜጎች የልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ተብራርቷል።

በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ዋና መሥሪያ ቤት እየተካሄደ በሚገኘው በዚህ የውይይት መድረክ ላይ፣ የፎረሙ አባላት በሀገራዊና ቀጠናዊ ተጨባጭ ሁኔታዎች ላይ በመወያየት የጋራ ግንዛቤ ይይዛሉ።

በቀጣይም የጸጥታ ስራውን በላቀ ስኬት ለመምራት የሚያስችሉ የጋራ ስምምነቶች ላይ እንደሚደረስ ይጠበቃል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል እና የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር አበበ ውቤ በፎረሙ ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top