የትንሳኤ በዓል በሰላም መጠናቀቁ የፖሊስና የህዝብ ቅንጅት ውጤት መሆኑ ተገለጸ
የዘንድሮው የትንሳኤ በዓል በመላው የአማራ ክልል በሚገኙ ሁሉም አካባቢዎች ያለምንም የፀጥታ ችግር በታላቅ ድምቀትና በሰላም መጠናቀቁን የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ እንደገለጸው በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ የክልሉ የጸጥታ ኃይል ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የሰራው ውጤታማ ስራ ለስኬቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብሏል።
የክልሉ ፖሊስ በዓሉን አስመልክቶ አስቀድሞ ዝርዝር ዕቅድ በማውጣትና ጥብቅ የጸጥታ ስምሪት በማድረግ የህዝቡን ደህንነት ለማስጠበቅ በከፍተኛ ቁርጠኝነት መሰማራቱንም ጠቅሷል።
ፖሊስ ከበዓሉ ዋዜማ ጀምሮ ማንኛውንም የጸጥታ ስጋት አስቀድሞ ለመከላከልና ወንጀልን ለመግታት በንቃትና በቁርጠኝነት መሰማራቱን የጠቀሰው ዋና ጠቅላይ መምሪያው የፖሊስ ዝግጁነት ከህብረተሰቡ የሰላም ባለቤት እኔ ነኝ ባይነት ጋር ተዳምሮ በዓሉ ያለምንም እንከን እንዲጠናቀቅ ማስቻሉንም አረጋግጧል።
የጸጥታ ኃይላችን የተሰጠውን ግዳጅና ስምሪት በከፍተኛ የዲሲፕሊን መንፈስና በቁርጠኝነት በመወጣቱ በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ አድርጓል፤ ይህም ሊመሰገን የሚገባው ውጤታማ ስራ ነው ሲል ዋና ጠቅላይ መምሪያው ገልጿል።
የፀጥታ ኃይሉ የተሰጠውን ግዳጅ በሚገባ ከመወጣቱም በላይ፣ ከህብረተሰቡ የቀረበለትን ጥቆማና መረጃ በአግባቡ በመተግበር ማንኛውንም የፀጥታ ክፍተት እንዳይፈጠር አድርጓል።
እንደ ዋና ጠቅላይ መምሪያው ገለጻ በዓሉ በስኬት እንዲጠናቀቅ የግል ምቾታቸውን መስዋዕት በማድረግ፣ ሌት ተቀን በመስክ ላይ ተሰማርተውና ድካምን ሳይፈሩ ለህዝብ ሰላም ሲሉ ፅናትና ሙያዊ ብቃታቸውን ላሳዩ የጥምር የፀጥታ ኃይል አባላት፣ አጠራጣሪ ነገሮችን ለጸጥታ አካላት በወቅቱ በማሳወቅና ከፖሊስ ጎን በፅናት በመቆም የማይተካ አጋርነት ላሳየው ለመላው የክልላችን ህዝብ፣ በበጎ ፈቃደኝነት ከፖሊስ ጋር ተቀናጅቶ በመስራት ከፍተኛ ተነሳሽነት ላሳዩ ወጣቶች እንዲሁም ሰላምን በመስበክና ህዝቡን በማረጋጋት ረገድ የማይተካ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የሃይማኖት አባቶች ላቅ ያለ ምስጋና አቅርቧል።
የሰላም ጉዳይ የአንድ ወገን ስራ ብቻ ሳይሆን የጋራ ውጤት መሆኑን አፅንኦት የሰጠው ዋና ጠቅላይ መምሪያው አሁንም በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ የተመዘገበው ድንቅ የቅንጅት ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስቧል።
በበዓሉ ወቅት የታየው ቅንጅታዊ አሰራርና የህዝብና ፖሊስ ትስስር በቀጣይም የክልሉን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ ትልቅ አቅም የሚሆን በመሆኑ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጧል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ
በጀግንነት መጠበቅ፤ በሰብዓዊነት ማገልገል!

