“በሚያልፍ ቀን የማያልፍ የታሪክ አሻራ አኑራችኋል!” ረዳት ኮሚሽነር አያልነህ ተስፋዬ
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የአስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያ ከፍተኛ አመራሮች የፋሲካን በዓል ምክንያት በማድረግ፣ የክልሉን ሰላም ለማስጠበቅ የአካል መስዋዕትነት የከፈሉ የፀጥታ አካላትን በባህር ዳር ፈለገ ሕይወት ሪፈራል ሆስፒታል በመገኘት ጎበኙ።
በቦታው ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽንና የአስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ረዳት ኮሚሽነር አያልነህ ተስፋዬ የክልላችንን ሰላም ለማደፍረስ ብሎም ሀገራችንን ለመበተን ከምንጊዜም ጠላቶቻችን ጋር በማበር የሚንቀሳቀሱ አፍራሽ አካላትን ፊት ለፊት በመጋፈጥ ሰላምን አያጸናችሁ የምትገኙ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ናችሁ ብለዋል።
“እናንተ በዚህ በሚያልፍ ቀን ለአማራ ሕዝብ ሰላምና ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት መከበር የማያልፍ ወርቃማ ገድል በመፈፀም ደማቅ ታሪክ የጻፋችሁ ጀግኖች ናችሁ” ብለዋል።
ረዳት ኮሚሽነር አያልነህ አክለውም፣ ጀግኖቹ ሀገርን ከመፍረስና ሕዝብን ከመበተን ለመታደግ በገቡት ቃል ኪዳን መሰረት መስዋዕትነት በመክፈላቸው የክልሉ መንግስትና ሕዝብ ኩራት እንደሚሰማቸው ገልጸዋል።
ለነዚህ ጀግኖች የሚሰጠው ክብር በቃላት ብቻ እንደማይወሰን በመጥቀስ፣ በደብረ ብርሃን ከተማ “የጀግኖች ማዕከል” እየተገነባ መሆኑን ይፋ አድርገዋል።
የሚገነባው ማዕከልም ከማገገሚያነት ባለፈ ራስን ለመቻል የሚያግዙ የሙያ ስልጠናዎች የሚሰጡበትና ለአባላቱ ዘላቂ ድጋፍ ለማድረግ ታስቦ የሚገነባ መሆኑን ጠቁመዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የሰው ሀብት አስተዳደርና ልማት ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር አብዮት ሽፈራው፣ የፀጥታ አባላቱ የሕዝብን አደራ በብቃት የተወጡ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በችግሮች ሳትበገሩ ያለፋችሁ፣ እንደ ወርቅ በእሳት ተፈትናችሁ ለግዳጅ የበቃችሁ በመሆናችሁ ክልሉ ዘላለማዊ አሻራችሁን ይዘክራል ሲሉ አወድሰዋል።
ጉብኝት የተደረገላቸው የፀጥታ አባላት በበኩላቸው፣ አመራሮቹ በበዓል ቀን በአካል ተገኝተው ላደረጉላቸው የሞራል ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
እንዲህ ዓይነቱ ተግባር ተቋሙ ለሰራዊቱ ያለውን ከፍተኛ ክብር እንደሚያሳይና በሰራዊቱ መካከል ያለውን ቁርኝት ይበልጥ እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።
በመጨረሻም የክልሉ ፖሊስ አመራሮች ለሀገር ሰላምና ደህንነት ሲባል በተለያዩ ግንባሮች መስዋዕትነት እየከፈሉ ለሚገኙ የክልሉና የፌዴራል የፀጥታ አካላት በሙሉ እንኳን ለፋሲካ በዓል አደረሳችሁ የሚል የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፈዋል።








