“የትንሳኤ በዓል ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከሞት ወደ ሕይወት የተሻገርንበት የድል፣ የፍቅርና የይቅርታ በዓል ነው” ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር)
ነገ እሁድ ሚያዚያ 04 ቀን 2018 ዓ.ም የሚከበረውን የትንሳዔ በዓል ምክንያት በማድረግ፣ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ/ር)
ያስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት
በመጀመሪያ የክፉ ቀን ደራሽ፣ የጭንቅ ጊዜ መከታ ለሆናችሁና የሕዝባችንን ሰላም ለማረጋገጥ በጽናት ለቆማችሁ የሰላም አምባሳደሮች የክልላችን የፖሊስ አባላትና የጸጥታ ኃይሎች፣ የጥምር ጦሩ አባላት እንዲሁም ለመላው የአማራ ሕዝብ፣ ለክርስትና እምነት ተከታዮች ኢትዮጵያውያን በሙሉ እንኳን ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሳኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ!
የትንሳኤ በዓል ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከሞት ወደ ሕይወት የተሻገርንበት የድል፣ የፍቅርና የይቅርታ በዓል በመሆኑ በደስታና በአንድነት የምናከብረው በዓል ነው ።
የትንሳኤ በዓል ለሁላችንም አዲስ ተስፋን፣ አንድነትንና መተሳሰብን ይዞልን እንደሚመጣ ሙሉ እምነቴ ነው።
ይህ በዓል ለዘመናት የቆየውንና የማንነታችን መገለጫ የሆነውን የመተሳሰብ፣ የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህላችንን ይበልጥ የምናድስበት ወቅት ነው።
ውድ የክልላችን ነዋሪዎች ክልላችን አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም እንዲኖረው፣ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥና ሕዝባችን በነፃነት ወጥቶ እንዲገባ የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ሌት ተቀን እየሰራ ይገኛል።
ሰላም የሁሉ ነገር መሠረት እንደመሆኑ መጠን፣ በበዓላት ወቅትም ሆነ በሌሎች የሥራ ቀናት የጀመርነውን የሰላም ጉዞ ለማስቀጠል የሕዝባችን ትብብርና ደጀንነት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።
ይህን ታላቅ በዓል ስናከብር የተቸገሩትን በመርዳት፣ የታመሙትን በመጠየቅና ካለን ላይ ለሌላቸው በማካፈል የኢትዮጵያዊነት ዕሴታችንን ልናሳድግ ይገባል።
የትንሳኤው ብርሃን በልባችን ፍቅርን፣ በቤታችን ሰላምን፣ በክልላችንና በሀገራችን ደግሞ ብልጽግናን እንዲያሰፍን ምኞቴ ነው።
የህዝባችንን ሰላም ለማስከበርና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በየግንባሩና በየመደበኛ የሥራ ስምሪቱ መስዋዕትነት እየከፈላችሁ የምትገኙ የፀጥታ ኃይሎች በሙሉ ለዝግጁነታችሁ ያለኝ አክብሮት ላቅ ያለ ነው።
በዓሉ በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ እያከናወናችሁት ያለው ተግባር የሚደነቅ ነው።
የህዝባችንን ደህንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥና በበዓሉ ወቅት ሊከሰቱ የሚችሉ የጸጥታ ስጋቶችን ለመከላከል ወትሮም የነበረው ዝግጁነታችሁ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስባለሁ።
ውድ የክልላችን ህዝቦች ከአካባቢያችሁ የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ለሰላም የምታደርጉትን ትብብር አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ ጥሬን አቀርባለሁ።
በመጨረሻም በዓሉ የሰላም፣ የጤና እና የደስታ እንዲሆንላችሁ እየተመኘሁ፤ በበዓል ወቅት ለሕዝብ ሰላምና ደህንነት በየፍተሻ ኬላዎችና በየቀጠናው ተሰማርታችሁ መስዋዕትነት እየከፈላችሁ ለምትገኙ የፖሊስ አባላት በሙሉ ያለኝን አክብሮት እገልጻለሁ።
በድጋሚ እንኳን ለትንሳኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ በዓሉ የሰላም፣የደስታ ፣የመተሳሰብና የመረዳዳት በዓል ይሁንልን!
በጀግንነት መጠበቅ፤በታማኝነት ማገልገል!
ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ (ዶ/ር) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ
ሚያዚያ 2018 ዓ.ም
ባህር ዳር ፣ኢትዮጵያ

